10/04/2026
ዛሬ ዓለም ሁሉ ዝም የሚልበት፣ የሰው ልጅ ታሪክ የተቀየረበት ታላቅ ቀን ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኔና ስለ እናንተ ፍቅር ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠበት፣ ያ ያማረው ፊቱ በጥፊ የተመታበት፣ ክብሩን ጥሎ እኛን ለማክበር በመስቀል ላይ የዋለበት ዕለት ነው።
#"ከዚህ_የሚበልጥ_ፍቅር_የለም..."
ወዳጆቼ ሆይ! እርሱ የሞተው እንድንኖር ነው። የቆሰለው እንድንፈወስ ነው። የተናቀው እኛ እንድንከበር ነው። ዛሬ ይህንን ቀን ስናስብ ግን በለቅሶና በሀዘን ብቻ መሆን የለበትም። ትልቁ የመስቀሉ ዋጋ የሚከፈለው በሕይወታችን ነው።
#ባለ_እዳዎች_ነን!
የከፈለልንን የሕይወት መስዋዕትነት በገንዘብ ወይም በቃላት ብቻ ልንመልሰው አንችልም። ለእርሱ የምንሰጠው ትልቁ ምላሽ ነው።
እርሱ እንደወደደን በመዋደድ፣
እርሱ ይቅር እንዳለን ይቅር በማለት፣
እርሱ ራሱን ዝቅ እንዳደረገ በትህትና በመመላለስ...
የእርሱን ሕይወት በውስጣችን ስናሳድግ፣ የመስቀሉ መስዋዕትነት በእኛ ሕይወት ላይ ፍሬ ማፍራት ይጀምራል። ዛሬ እንዲህ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፦ "ለእኔ የሞተልኝን ጌታ፣ እኔስ እንዴት እየኖርኩለት ነው?"
"እንግዲህ በሕይወት የሚኖሩት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።" (፪ኛ ቆሮንቶስ ፭፥፲፭)
የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በልባችን ይንገስ። የመስቀሉ በረከት በሁላችንም ላይ ይሁን!
#መልካም_የስቅለት_መታሰቢያ_በዓል