08/07/2022
"የተሰራልኝ ኦፕሬሽን ምን እንደነበር እና ለምን እንደ ተሰራልኝ አላውቀውም!"
ከተለመዱት የአዳር የስራ ፕሮግራሜ በአንዱ ነው... አንድ በ40 ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ጎልማሳ በጠና ታሞ ወደ ቀዶ ህክምና ድንገተኛ ህክምና ክፍል መምጣቱ ተነግሮን እሱን ለማየት ሄድን።
ገና ሲታይ በጽኑ ህመም መታመሙ ያስታውቃል። ያቃስታል...ሆዱ በጣም ከመቆዘሩ የተነሳ የደረሰች ነፍሰ ጡር አስመስሎታል። ቀርበን ካየነው በኋላ መደ መመርመርያ ክፍል አስገብተን ጫጫታ በሌለበት ሁኔታ ስለ ህመሙ ሁኔታ መጠየቅ ጀመርን። ህመሙ ሦሥት ቀን እንደሆነው ...በእነዚህ ቀናትም... እያደር የሆዱ መቆዘር እና ቁርጠት እየጨመረ መምጣቱን በተያያዘም እንደሚያስመልሰው እና ሰገራም ሆነ ፈስ እንዳልወጣው ነገረን። ሌሎች አስፈላጊ ምልክቶች እንዳሉት እና እንደሌሉት ከጠየቅን በኋላ.... ሰውነቱን ለመመርመር ልብሱን እንዲገልጥ ጠይቀን ምርመራው ተጀመረ። ሆዱ ላይ ቁልቁል በእንብርቱ የሚያልፍ የቆየ የኦፕሬሽን የሚመስል ጠባሳ አለ። የበፊቱ ኦፕሬሽን በሌላ ሀስፒታል የተሰራ በመሆኑ አሁን ስለያዘው በሽታ ምንነት ለማወቅ ፍንጭ ስለሚሰጠን እንደገና መጠየቅ ጀመርን።
"ይሄ መቼ የተሰራ ኦፕሬሽን ነው?"
" የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ነው" አለ እያቃሰተ።
" በምን ምክንያት ነበር የተሠራው ኦፕሬሽኑ?" ቀጣዩ እና አስፈላጊው ጥያቄ ተጠየቀ።
"እሱን አላውቀውም.... ብቻ ያኔም እንዳሁኑ ሆዴን በጣም ታምሜ ነው በድንገተኛ የተሰራልኝ" አለ የምርመራ አልጋው ላይ እየተገላበጠ።
" ስለ ህመሙ ምንነት ተነግሮህ ነበር?....ከኦፕሬሽኑ በኋላስ ለምርመራ የተላከ ናሙና ነበር? ...... የዛን ጊዜም ካሁኑ ህመምህ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች ናቸው የነበሩት?...ወዘተ "
ስለ በፊቱ ኦፕሬሽን ብዙ ጥያቄዎችን አከታትለን ብንጠይቅም...ከታማሚውም ሆነ ከአስታማሚዎቹ በቂ መረጃ ማግኘት አልቻልንም ነበር። አሁን ስላለው ህመሙ ለማወቅ ትልቁን እና ዋናውን መረጃ ማግኘት ሳንችል ቀረን። የአካል ምርመራውን ከጨረስን በኋላ አስፈላጊ የራጅ እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን ልከን ኦፕሬሽን የሚያስፈልገው ህመም ነበር እና በዚህም ከተስማማን በኋላ ይዘነው ወደ ኦፕሬሽን ገባን።
ለመሆኑ ....
1. አንድ ታካሚ ኦፕሬሽን ሊሰራለት ሲወሰን ስለ በሽታው ምንነት የመጠየቅ መብት አለው?
2. ኦፕሬሽን ለምን እነደሚሰራለት እንዲሁም ኦፕሬሽን ባይሰራ ሌላ የህክምና አማራጭ እንዳለው የመጠየቅስ መብት አለው?
3. ኦፕሬሽኑን ተከትሎ ሊመጡ ስለሚችሉ ተያያዥ ችግሮችስ ማብራርያ ሊደረግ ይገባል?
4. ኦፕሬሽኑን የሚሰራው ባለሞያስ ስለ በሽታው እና ስላሉት የህክምና አማራጮች እንዲሁም ተያይዘው ስለሚመጡ ችግሮች ለታካሚው እና ቤተሰቡ ማብራርያ የመሰጠት ግዴታ አለበት?
እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች የሚመልስልን ማንኛውም ኦፕሬሽን (መለስተኛም ሆነ ከባድ) ከመሰራቱ በፊት በኦፕሬሽን ባለሞያው እና በታካሚው( ቤተሰቡ) መኃል የሚደረገው የስምምነት ቅጽ(Consent form) ነው።
ይህ የስምምነት ቅጽ በተለያዩ ሆስፒታሎች መጠነኛ የይዘት ልዩነት ቢኖረውም ከሞላ ጎደል ወሳኝ በሆኑ ነጥቦች ላይ ሁሉም ተመሳሳይ ይዘት አላቸው።
የቅድመ ኦፕሬሽን የስምምነት ቅጽ ታካሚው እና ቤተሰቡ በቅጹ ላይ ከመፈረማቸው በፊት መሞላት ያለበቸውን አስፈላጊ ጥያቄዎችን ይይዛል። ከእነዚህም መኃል የሚከተሉት ይገኙበታል።
፨ ኦፕሬሽኑ የሚሰራለት ታካሚ ስም....
፨ ኦፕሬሽኑን የሚሰራው ባለሞያ/ዎች ስም....
፨ ታካሚው(ቤተሠቡ) ስለ በሽታው ምንነት ያውቃሉ ወይስ አያውቁም ......
፨ በሽታው ምንድን ነው....
፨ ኦፕሬሽኑ የሚሰራው በምን ምክንያት ነው? .....
፨ በኦፕሬሽኑ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?...
፨ ከኦፕሬሽን ውጪ ሌላ የህክምና አማራጭ አለው ወይ? ....
፨ ኦፕሬሽን ባይሰራ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ምን ምን ናቸው?....
፨ በኦፕሬሽኑ ሰዓት ታካሚው ደም ቢያስፈልገው ለመውሰድ ፈቃደኛ ነው ወይ?...... እና ወዘተ
ማንኛውም ታካሚ ድንገተኛም ሆነ ድንገተኛ ላልሆነ ህመም፤ መለስተኛም ሆነ ከባድ ኦፕሬሽን ከማሰራቱ በፊት ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ኦፕሬሽኑን ከሚሰራው ባለሞያ ጠይቆ የመረዳት መብት አለው። ባለሞያውም ስምምነቱን ከማስፈረሙ አሥቀድሞ እነዚህን እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ለታካሚው እና ቤተሰቡ የማስረዳት ግዴታ አለበት። ይህን ማድረጉ አሁን አሁን እየታየ ያለውን በታካሚ እና በባለሞያው መኃል ያለ አለመተማመን.... እና አስፈላጊም ሆነ አላስፈላጊ መወነጃጀል ሊቀንስ ይችላል። በተለምዶም ከህክምናው በኋላ የሚከሰቱ ችግሮችን ታካሚው እና ቤተሰቡ... እንዲሁም ዩቲዩበሮች... "የህክምና ስህተት ነው" እያሉ ጣታቸውን ወደ ባለሞያው እንዳይቀስሩ የራሱ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በማንኛውም መለስተኛም ሆነ ከባድ ኦፕሬሽን ወቅት የታካሚውን እና ቤተሰቡን መልካም ፈቃድ ያማከለ ኦፕሬሽን መሰራት እንዳለበትም ግንዛቤን ይፈጥራል።