Ethio-Lab Page

Ethio-Lab Page Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Ethio-Lab Page, Medical Lab, Addis Ababa.

This page is created by members of Ethiopian Medical Laboratory Professionals to serve as an outlet for activities performed in the health facilities, research institutes, and universities.

15/02/2021

የኮሮና ክትባት ተስፋዎች፣ ስጋትና ፖለቲካ
==================

ምዕራባውያን 5 ሃያል የሆኑ የኮሮና መከላከያ ክትባቶችን ሰርተናል አሉ፡፡ የመከላከል አቅማቸውም ቫይዘር 95 %፣ ሞደርና 94.8 % እና አሰትራ ዜኒካ 70.4 % ወዘተ ነው አሉን፡፡

የአሰትራ ዜኒካን ክትባት በደቡብ አፍሪካ ለተነሳው አዲሱ ዝርያ መከላከያነቱ/ፈዋሽነቱ 10-25 % ብቻ ነው ተባለ፡፡ የጆንሰን ጆንሰንም፣ የኖቫቫክስም በአድሱ የደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስ ዝርያ(B.1.351 ወይም 501.V2),) ውጤታማነታችው አነስተኛ ናቸው፡፡ የጆንሰን ጆንሰን ክትባት ቀላል የህመም ምልክቶችን ለማስቀረት አቅሙ 57 % ሲሆን፤ ናቫቫክስ ደግሞ 49 % ነው፡፡

የአሰትራ ዜኒካን ክትባት ምርምርና ስርጭት የምትመራው ጊልበርት፣ እየቀባጠረች ነው፡፡አስትራ ዜኒካ በእንግሊዝ የተነሳውን አዲሱን ቫይረስ (B.1.1.7) ጨምሮ በጥሩ ብቃት እንደሚከላከል ቢገልፁም መረጃው ላይ በርካታ ብዝታዎች አሉ፡፡ የዚህ ክትባት በአዲሱ የእንግሊዝ ዝርያ ላይ ያሳየው ውጤታማነት 21.9% ብቻ ነው፡፡

የካቲት 21/2021 የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት ሀገራት በትብብር ለመስራት እያሳዩት ያለው ዳተኝነትና የራሴን ዜጋ ብቻ የሚለው የበቀል አካሄዲ ወረርሽኙ ያሉትን ክትባቶች እንዲላመዳቸው ያደርጋል እንጅ መፍትሔ አይደለም እያሉ ነው፡፡ የራስህን ዜጋ ከትበህ ሌላውን መተው ከሞራል አንፃርም ትክክል አይደለም፡፡

በአንድ ጥናት መረጃ መሰረት ክትባት ያላቸው ሀገሮች የራሳቸውን ዜጋ ቢከትቡና ክትባት የሌላቸው ሀገራት ቤታቸውን በመዝጋት ከቤታቸው ቢቀመጡ፣ ሀብታም ሀገሮች እስከ 4.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚከስሩ ያመለክታል፡፡

አሁን በክትባት እየታየ ያለው የእኔ ዜጎች ብቻ ይከተቡ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አርቲፊሻል የእቃ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሀብታም ሀገራት ከራስ ፍላጎት በላይ ላለማምረት እያሳዩት ያለው ዳተኝነት፣ ተጨማሪ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳና ትርፍ የለውም፡፡

እስከሁን ድረስ ከ30000 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሞተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ዘንዶው ኢቦላ ቫይረስ እንደተነሳ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ የአደገኛ ጀርሞች ጭፈራና ፉከራና የአለም ዲንቀርና አስፈሪ ነው፡፡

የሰው ልጅ የዘረ-መል ጥናት ፕሮጀክት===================የመጀመሪያውና ታላቁ የሳይንስ ምርመር የተባለው የሰውን ዘረ-መል የመደርደር ስራ ነበር፡፡ ይህም በ1990 (እ.ኤ.አ) ተጀመ...
13/02/2021

የሰው ልጅ የዘረ-መል ጥናት ፕሮጀክት
===================

የመጀመሪያውና ታላቁ የሳይንስ ምርመር የተባለው የሰውን ዘረ-መል የመደርደር ስራ ነበር፡፡ ይህም በ1990 (እ.ኤ.አ) ተጀመሮ በ2001 የመጀመሪያው ድራፍት ተጠናቋል፡፡ 2021 20ኛ የጉዞ አመታትን የገመገመው ኔቸር-መጽሔት ጠቅለል ያለ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡
በዚህ በ20 ዓመታት ጉዞው የሰው ልጅ ካሉት ከ30,000 በላይ የሚሆኑ በራሄዎች ውስጥ በስፋት የተጠኑትና የታወቁት ከ8 አይበልጡም፡፡ እስከ 2017 ባለው ጊዜ የተሰሩ ስራዎችን በምንመለከትበት ሰዓት 22 ፐርሰንት የሚሆኑት የዘረ-መል ጥናቶች ያተኮሩት 1ፐርሰንት በሚሆኑት በራሄዎች ላይ ነው፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከታወቁት ውስጥ TP53 (9232 ምርምሮች ታትመውበታል), TNF, EGFR፣ TL6, VEGFA, APOE, TGFB1… የሚባሉት በራሄዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

ሲጠቃለል በርካታ ስራዎች ቢሰሩም፣ ሳይንስ የሰው ልጅ የዘረ-መል ስሪትን ለማወቅ የጀመረው ጉዞ ገና በጭልፋ የመቅመስ ያክል እንጅ ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡

የሰው ልጅ ከባህርም ከውቅያኖስም፣ ከህዋም በላይ የማይታወቅ አስገራሚ ፍጥረት ነው፡፡ ክብር ሰውን ለፈጠረ ፈጣሪ

A new analysis traces the story of the draft genome’s impact on genomics since 2001, linking its effects on publications, drug approvals and understanding of disease.

02/02/2021

ትክክለኛው የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የሙያ ስያሜ
================

1.ረዳት ላቦራቶሪ (medical laboratory assistant)፡ በህክምና ላቦራቶሪ ሰርተፈኬት ያላቸው

2.ላቦራቶሪ ቴክኒሻን (Medical laboratory Technician)፡ በህክምና ላቦራቶሪ ዲፕሎማ ያላቸው

3.ላቦራቶሪ ቴክኖሎጅስት (Medical lab technologist/medical technologist)፡ በህክምና ላቦራቶሪ የመጀመሪያ ድግሪ ያላቸው

4.ላቦራቶሪ ሳይንቲስት (Medical Laboratory Scientists)፡ በአንዱ የላቦራቶሪ ት/ት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው

5.ላቦራቶሪ ስፔሻሊስት (certified Medical Laboratory Scientists)፡ በእንዱ የህክምና ላቦራቶሪ ዘርፍ ፒ-ኤች-ዲ-ዲግሪ ያላቸው

+++++++++++++++++++
ስፔሻሊቲ የላቦራቶሪ የት/ት ዘርፎች በከፊል
++++++++++++++++++++

1) ህክምና ማይክሮባዮሎጅ (ባክቴሪዎሎጅ፣ ቫይሮሎጅ፣ ማይኮሎጅ፣ ማይክሮቢያል ጄኔቲክስ…)

2) ህክምና ፓራሲቶሎጅ (ሄልመንቶሎጅ፣ ፕሮቶዞሎጅ፣ ቬክተር ቦርን በሽታዎች፣ ማላሪሎጅ…)

3) ኢሚኖሎጅ (ቫክሲኖሎጅ፣ ክሊኒካል ኢሚኖሎጅ፣ አለርጅ፣ሪሄማቶሎጅ…)

4) ሄማቶሎጅ ( ኢሚኖ ሄማቶሎጅ፣አነሚያ፣ ሊኬሚያ…)

5) ክሊኒካል ኬሚስትሪ (ኢንዶክሪኖሎጅ፣ ቶክሲኮሎጅ…)

6) ላቦራቶሪ ማናጅመንት

----------------------------------
Written by:

Menberu Fitsum (Amhara Regional Health Bureau) and Admin
-----------------------------------------

የኮቪድ-19 አንቲቦዲ መመርመሪያ መሳሪያዎች ጥራትና ብቃት፡ የምርምሮች ጭምቅ ውጤትና ትንተና             ============================በ2019 (እ.ኤ.አ) የተነሳውና ...
23/01/2021

የኮቪድ-19 አንቲቦዲ መመርመሪያ መሳሪያዎች ጥራትና ብቃት፡ የምርምሮች ጭምቅ ውጤትና ትንተና
============================

በ2019 (እ.ኤ.አ) የተነሳውና ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ፤ ኮቪድ-19 የተባለ ደረቅ የሳንባ ምች በሽታ በማምጣት የአለም ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ኮሮናቫ ይረስ በሚለው ዝርያ ውስጥ 7 ዓይነት የሰው በሽታ አምጭ ኮሮና ቫይረሶች የሚታወቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አዲሱ ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 ከሁሉም ኮሮና ቫይረሶች በከፋ መልኩ በጣም ተላላፊ ቫይረስ ነው፡፡ በጆንሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ የበይነ መረብ መረጃ ቋት መሰረት 98 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ሲታመሙ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የአለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስር ባህሪዎች እየተቀየሩ ናቸው፡፡
---
በእያንዳንዱ ሰው ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ምርመራ ለማድረግ አለም እየተጠቀመበት ያለው የላቦራቶሪ መሳሪያ የቫይረሱን ዘረ-መል መሰረት ያደረገ RT-PCR የሚባል መሳሪያ ነው፡፡ ይህ መሳሪያ በአለም የጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውና የአለም የጤና ድርጅት በሚያስተዳድራቸው ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ መሳሪያ ቢሆንም፤ በርካታ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ከጉድለቶቹ መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
1. ከጉሮሮ ወይንም አፍንጫ ውስጥ የሚወጡ ፈሳሾችንን የሚጠቀም ስለሆነ በናሙና አወሳሰድ ላይ ስህተት ከተፈጠረ ውጤቱ ትክክለኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ ቫይረሱ እያለ የለም የማለት ባህሪ ያሳያል፡፡
2. መሳሪያው ውድና በቂ ክህሎት ባላቸው የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ብቻ የሚሰራ መሆኑ፣ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ አስቸግሯል፡፡
3. መሳሪያው በየጊዜው የጥራት ሁኔታው መፈተሽ አለበት፣ ለዚህ ተብሎ የሚዘጋጀው ኬሚካል ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ እጥረት ይታይበታል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ጥራቱን ጠብቆና አገልግሎቱ ሳይቆራረጥ ለመስራት ትልቅ ተግዳሮት ነው
4. ቫይረሱ ዘረ-መሉን ሊቀይርና ከመመርመሪያው መሳሪያ እይታ ውጭ በመሆን የተሳሳተ ውጤት ሊያወጣ ይችላል፡፡
5. ከዚህ በተጫመሪ ምርመራው በራሱ አድካሚና ቀናትን የሚወስድ ነው፡፡
ስለሆነም በ15 እና በ30 ደቂቃ ውስጥ ውጤት የሚሰጡ፣ በትንሽ ስልጠኛ ከላቦራቶሪ ባለሙያዎች ውጭ ያሉ ሰዎች ጭምር ሊጠቀሙበት የሚችል፣ የጥራት ደረጃቸው አስተማማኝ የሆነ፣ ከጉሮሮና አፍንጫ ሳይሆን በደም ናሙሳ መስራት የሚችሉ፣ በሽታው የቅርብ ጊዜና የሩቅ መሆኑን መለየት የሚችሉ፤ ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያዎች መስራትና ገበያ ላይ ማዋል የአለም የመጀመሪያውና ከፍተኛው ፍላጎት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ፍላጎቶች ሊያሟሉ የሚችሉ መሳሪዎችን ለማምረት በርካታ ኩባንያዎችና የዩንቨርሲቲ የምርምር ላቦራቶሪዎች በሽቅድድም ላይ ነበሩ አሁንም ናቸው፡፡ በመሆኑም ወረርሽኙ በገባ በወራት ውስጥ በርካታ ኩባንያዎች ጥራት ያለው ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያ/ኪት/ ሰርተናል በማለት ምርታቸውን በተለያዩ ሀገራት እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ የጥራት ተቆጣጣሪ ጅርቶችና የአለም የጤና ድርጅትም እውቅና እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም እነዚህን እንደ አሸን የፈሉ የመመሪመሪያ መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸውን መፈተሽ፣ አንድም መርጦ ለመጠቀም በሌላ መልኩ የጥራት ጉድለት ያለባቸው መሳሪያዎች ገበያዉን ሰብረው በመግባት ፈቃድ እንዳያገኙና የጤና ስርዓቱን እንዳይጎዱት ሳይንሳዊ ፍተሻና ቁጥጥር ማደረግ ያስፈልጋል፡፡
---
የእኛ የምርምር ቡድን፣ በአለም ላይ በተለያዩ ካምፓኒዎችና የምርምር ተቋማት የተሰሩትን የኮቪድ-19 ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያዎች ላይ የጥራት ፍተሻ ያደረጉ ምርምሮችን ወደ አንድ በማምጣት ጭምቅና ድምር ውጤታቸው ምን እንደሚመስል ማየት ነው፡፡ የተሰሩት ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያዎች ጥራት የተፈተሸዉ ደግሞ በመሳሪያዎቹ አይነት፣ የተጠቀሙትን የአንቲጅን አይነትና የአንቲቦዲውን አይነት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
------------------------
ውጤት
----------------------
በ8 ሀገራት የሚገኙ የ47 ካምፓኒዎችን ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያዎች የጥራት ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ የያዙ 24 የምርምር ስራዎች ማገኘት ችለናል፡፡ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በሶስት ዋና ዋና አይነቶች የሚመደቡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እነሱም በኢንዛይም የሚሰራ ኢላይዛ (Enyme-linked immunosorbent assay)፣ በኬሚካል የሚሰራ ኢላይዛ መሳይ መመርመሪያ( Chemiluminescence immunoassay) እና አር-ዲ-ቲ (Colloidal-gold lateral-flow immunoassays) ናቸው፡፡
ከሶስቱ መካከል በኬሚካል የሚሰሩት የመመርመሪያ አይነቶች የተሻሉ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሆነው ተግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ በRT-PCR ፖዘቲቭ የሆኑ 100 የኮቪድ-19 በሽተኞች በአዲሱ መሳሪያ ሲሰራላቸው በአማካይ 92% (95% CI: 86-95%)ቱን ፖዘቲቭ ሲል 8 ሰዎችን በስህተት የለባቸውም/ኔጌቲቭ ናቸው የማለት ባህሪ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በRT-PCR ተመርምረው የለባችሁም የተባሉትን 100 ሰዎች በዚሁ በአዲሱ መመርመሪያ ሲመረመሩ 99% (CI: 97-99%) ኔጌቲቭ ብሎ አንድን ሰው ግን በስህተት ኮቪድ-19 አለበት የማለት ባህሪ አሳይቷል፡፡ ስለሆነም የዚህ መሳሪያ sensitivity 92% (95% CI: 86-95%) ሲሆን specificity 99% (CI: 97-99%) ሆኗል (የሮክ ከርቭን ምስል ይመልከቱ)፡፡
በተመሳሳይ አገላለፅ በኢንዛይም የሚሰራው የኮቪድ-19 ኢላይዛ በሽታው አለ የማለት አቅሙ (sensitivity) 86% (CI: 82-89%) ሲሆን specificity ደግሞ 99% (CI: 98-100%) ነው፡፡ የአር-ዲ-ቲዎች ጭምቅ sensitivity 78% (CI: 71-83%) ሲሆን specificity 98% (95%CI: 96-99%) ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ከበርካታ የአንቲጅን አይነቶች መካከል RBD የተባለውን አንቲጅን የተጠቀሙ መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸውን በተወሰነ መልኩ ከፍ አድርጎት ይታያል፡፡ ከሶስቱ የአንቲቦዲ አይነቶች (IgA፣ IgM እና IgG) መካከል 3ቱን መሰረት አድርገው ለመመርመር የተሰሩት መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸው በተወሰነ መልኩ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተናጠል በምናይበት ሰዓት IgA መኖሩን ለማረጋገጥ የተሰሩት አንፃራዊ የተሻለ ጥራት እንዳላቸው ያሳያል፡፡ ነገር ግን ይህን አንቲቦድ መሰረት አድርገው የተሰሩት መሳሪያዎች ትንሽ በመሆናቸው፤ በትንሽ መረጃ ተነስተን የተሻለ ነው ለማለት ብዙ አያስደፍርምና ወደ ፊት ቢታሰብበት የሚል ምክር እንሰጣለን፡፡ IgM ወይንም IgG እንዲሁም ሁለቱን በተጠቀሙ መሳሪያዎች መካከል የሰፋ የጥራት ልዩነት አልታየም፡፡
ሲጠቃለል በኬሚካል የሚሰራው መመርመያ የተሻለ ሲሆን የኮቪድ-19 የአር-ዲ-ቲ መመርመሪያ አይነቶች ግን ከፍተኛ የሆነ የጥራት ችግር ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ይህ መረጃ ለአለም የጤና ድርጅት ቀድሞ የተሰጠ ሲሆን ድርጅቱ ከሁሉም አለም ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በስሩ የሚያስተዳድራቸውን የድሃ ሀገራት የጤና ስርኣትን አቅጣጫ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በራሳቸው መረጃና ኢኮኖሚ የሀገራቸውን የጤና ስርዓት የሚመሩ ሀገራት ግን እነዚህን መሳሪዎች እንደየ አስፈላጊነቱ ሊጠቀሙባቸው ይችላል፡፡
ይቆየን

በኮቪድ 19 ምክንያት ህይወቱ ያለፈው የሞያ አጋራችን የሆነው ወጣት አየናቸው በቀለ ጥር 6 ቀን 2013 የቀብር ሥነ-ስርዓት በመካኒሳ አቦ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ተፈፅሟል፡፡========...
22/01/2021

በኮቪድ 19 ምክንያት ህይወቱ ያለፈው የሞያ አጋራችን የሆነው ወጣት አየናቸው በቀለ ጥር 6 ቀን 2013 የቀብር ሥነ-ስርዓት በመካኒሳ አቦ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ተፈፅሟል፡፡
==========================================
አቶ አየናቸው በቀለ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቫይረስ ምርምር ዘርፍ ሲያገለግል የነበረ ወጣት የላቦራቶሪ ባለሞያ መሆኑን እየገለፅን ኢትዮ ላብ ፔጅ በሞያ አጋራችን ሞት የተሰማውን ሀዘን ይገልፃል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለሥራ ባልደረቦቹና ለቅርበ ወዳጆቹ መፅናናትን እንመኛለን፡፡
==========================================
Ethiopian Public Health Institute
EMLA / Ethiopian Medical Laboratory Association
Lia Tadesse, Minister of Health

21/01/2021

አንድ ሞኝ የተከለውን ሃምሳ ብልህ አይነቅለውም ይባላል
===================
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ተብሎ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ትካሻ ለትካሻ የመገጫጨት ሰላምታ ልማድ ሆኖ እንዳይቀር ያሰጋል፡፡

ከዚህ ምስል የሚታዩት የሰላምታ አይነቶች፡ ጤነኛ፣ ቀላልና መከባበርን የሚያሳዩ የሰላምታ አይነቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ኮሮና የሚባል ሞኝ የተከለው የሰላምታ አይነት ልማድ ሆኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡

የአመቱ በጎ ሰው!!!=========ሟች ጎንደር አርማጭሆ ማሰሮ ደንጎር በምትባል የገጠር ቀበሌ ተወልዶ ያደገ ምስጉንና ቅን አገልጋይ ነበር፡፡ የሟች ጓደኛ ደግሞ ከጎጃም ክፍለ ሀገር ነው፡፡ ...
13/01/2021

የአመቱ በጎ ሰው!!!
=========

ሟች ጎንደር አርማጭሆ ማሰሮ ደንጎር በምትባል የገጠር ቀበሌ ተወልዶ ያደገ ምስጉንና ቅን አገልጋይ ነበር፡፡ የሟች ጓደኛ ደግሞ ከጎጃም ክፍለ ሀገር ነው፡፡ ሁለቱም ቅንና ተግባቢ ስለነበሩ የሚተማመኑ ጓደኛሞች ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ እናማ የሟች ሚስት ወልዳ ለመታረስ ጎንደር፣ የሟች የጓደኛ ባላቤት ደግሞ ለትምህርት ወደ ዩነቨርሲቲ ሲሄዱ፣ ሁለቱ ጊዜያዊ ላጤ ሆነው፣ አብረው ዉለዉ አብረው የሚያድሩ ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ ሟች ከጨጓራ ጋር ተያይዞ ያመዉ ስለነበር ህመሙ እየጠናበት ሲመጣ፣ ወደ ጎንደር በማቅናት ከባለቤቱና ልጆቹ ጋር በመሆን እረፍት በመውሰድ እራሱን ዘና እያደረገ በሽታውን ለመቆጣጠር ቢሞክርም ሊሻለው አልቻለምና ጎንደር ሆስፒታል፣ ከዚያም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተንከራተተ፡፡ ከ6 ዙር በላይ ኬሞ-ቴራፒ ወሰደ ሊሻለው አልቻለምና የስልክ ግንኙነታቸው ቷቀረጠ፡፡

አንዷ ቅንና ባለራዕይ የስራ ባልደረባችን የደረሰ ጉዳይ እያሳሰበኝ ነዉ እባካችሁ ቶሎ ሄደን አይኑን እንየው ስትል የሰማዉ ይህ ቅን ጓደኛዉ ባለቤቱንና ጓደኞቹን በመያዝ የመጨረሻዋ ቀን ጎንደር ይገባል፡፡ ይች ቀን ለካም ወንድማችን ደረሰ የመጨረሻዋ ቀን ነበረችና ከቤቱ ስንደርስ አይደለም ሰው መለየት ቀርቶ በግዴታ ጠጣ እየተባለ የሚጋተውን የባህል መድሃኒት እንኳ መከላከል አቅቶት፣ ተውኝ እያለ እያለቀሰ አገኘነው፡፡የሚያውቀው ሰውነት ፈርሶ ከፍራሹ ጋር ተጣብቆ ሲያየው የዚህ ቅን ወንድም እምባ ሊቆም አልቻለም፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ከእንግዲህ ከእሱ ጋር ሳይሆን ያስረከበኝ የልጆቹ ጉዳይ ያሳስበኛል በማለት በሀሳብ ውስጥ ሆኖ ባህር ዳር እንደገባን አርፏል የሚል መርዶ ሰማን፡፡ ሳይነጋ ተመልሶ በመሄድ አፈር አልብሶ፣ የልጆቹንና የባለቤቱን እምባ አብሶ ተመለሰ፡፡

መልካምን ነገር ወደ ተግባር መቀየር ባህሪው የሆነው ይህ ቅን ጓደኛ ከጓደኞቹ የሰማቸውንና የራሱንና የባለቤቱን ሀሳብ ጨምሮበት፣ አካውንት በመክፈት ጓደኛየን ያጣሁ ወንድማችሁ ነኝ፡፡ እኔን የምትወዱኝ ከሆነ፣ የደረሰ ልጆችም የሚያሳዝኗቹህ ከሆነ ዛሬ እርዱኝ በማለት በፌስቡክና ቴሌገራም በመክፈት ተሯሯጠ፡፡ የበርካታ ቢሮዎችን ደች አንኳኳ፣ ከበርካታ ተሰብሳቢዎች ፊት ቆሞ አቤት አለ፡፡ ቅን የስራ ሰው ስለነበር አይደለም በሚሰራበት አማራ ክልል በመላ ኢትዮጵያ የእሱን ስም የማያወቅ የላቦራቶሪ ባለሙያ የለም፡፡ በአማራ ክልል ከተራ የጤና ጣቢያ ሰራተኛ እስከ ክልል ምክር ቤት በአካል ባያውቁት እንኳ በስም ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ጠይቆ አላፈረም፤ ካሰበው በላይ ተሳክቶለት ገንዘብ በማሰባሰብ የወደቁትን የጓደኛውን ቤተሰቦች መሰብሰብ ችሏል፡፡ መልካምነትን ወደ ሀብት በመመንዘር ከኪራይ ቤት አውጥቶ መጠለያ ገዝቶ አስገብቷቸዋል፡፡

የኢትዮ-ላብ ፔጅ አስተዳዳሪዎች ይህን ሰው የአመቱ በጎ ሰው ብለው እውቅና የሰጡት ሲሆን እውቅናውን ያገኘበት ምክንያት ደግሞ በሟቹ ጓደኛው ልጆች ስም እርዳታ በማሰባሰብ ኮንዶምንየም ገዝቶ በመስጠት ስላደረገው የላቀ ማህበራዊ ስራው ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የህብረሰተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበርና የኢትዮጵያ የህክምና ላቦራቶሪ ማህበር የአመቱ በጎ ሰው ብለው ቢሸልሙት ያንስበት ይሆናል እንጅ አይበዛበትም፡፡ ስለሆነም ይህን ጥቆማ አየሰጠን ስናስተዋውቃችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ ይህ ሰው ሙላቱ መለሰ ይባላል ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲት!! ከጎኑ ሆና በሀሳብ የምትደግፈው ባለቤቱ ደግሞ ማህሌት ወርቁ ትባላለች፡፡

ወንድማችን ሙላትና እህታችን ማህሌት እንኳን ያሰባችሁት ተሳካ!! ከደግ ሰው ጋር መዋል ምንኛ የህሊና እረፍትን ይሰጣል!!!፡፡ እኛም ከአንተ ብዙ መልካም ነገሮችን ተምረናልና እናመሰግናለን!!!

የሜቲሲሊንን መድሃኒት የተላመደ የስታፊሎኮከስ አወረስ ባክቴሪያ ስርጭት፡ ከኤች.አይ.ቪ ጋር ከሚኖሩ ህፃናት ላይMethicillin-resistant staphylococcus aureus among ...
12/01/2021

የሜቲሲሊንን መድሃኒት የተላመደ የስታፊሎኮከስ አወረስ ባክቴሪያ ስርጭት፡ ከኤች.አይ.ቪ ጋር ከሚኖሩ ህፃናት ላይ
Methicillin-resistant staphylococcus aureus among HIV positive Children
========================================

በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ ሜቲሲሊን የሚባለውን የመድሃኒት ዓይነት የተላመደ ስታፊሎኮከስ አወረስ የሚባለው የባክተሪያ አይነት መጠኑ እየጨመረና ለአለም አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በተለይም በኤች. አይ. ቪ የተያዙ ሰዎች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የችግሩ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያመላክት በቂ ጥናት አልነበረምና ይህንን ጥናት ለማካሄድ መነሻ ሆኖናል፡፡
-
የጥናቱ መረጃ የተሰበሰበው ከታህሳስ-የካቲት 2006 ዓ.ም ባለው ወቅት ሲሆን ጥናቱ የተካሄደውም በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ በተመረጡ የኤች አይ-ቪ ክሊኒኮች ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑና የኤች አይ-ቪ/አድስ ክትትል በሚያደርጉ ህፃናት ላይ ሆኖ ናሙና የተወሰደው ከአፍንጫ፤ ፊንጢጣና እጅ ላይ ነበር፡፡ ከ3ቱ ቦታዎች ናሙና ከተሰበሰበ በኋላ ካልቸር ሚድያ ላይ ተዘርቶ በ35 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠን ውስጥ ለ18 ሰዓታት ተቀምጧል፡፡ ከዚያ በኋላ ያደጉት ባክቴሪዎች እነማን ናቸው የሚለውን ለማወቅ የተለያዩ የመለያ ዘዴወችን ተጠቅመናል፡፡ በተለይ ስታፊሎኮከስ አወረስን ከሌሎች ለመለየት ልዩ የማሳደጊያ ሚዲያዎችን ተጠቅመናል፡፡ስታፊሎኮከስ አውሬስ ከተለየ በኋላ ከዚህ ባክቴሪያ መካከል የምን ያህሉ ሰው ሜቲሲሊን የተባለዉን መድሃኒት የተላመዱ ናቸው የሚለዉን ለማወቅ “Genotype MRSA VER 3.0” የተባለ ዘረ-መልን መሰረት አድርጎ ለምርመራና ምርምር የሚውል ኪት ተጠቅመናል፡፡
--
በዚህ ጥናት መሰረት ናሙና ከተወሰደላቸዉ 400 ህፃናት መካከል 126ቱ ስታፊሎኮከስ አወረስ የተባለዉ ባክተሪያ የተገኘባቸዉ ሲሆን፡ ከ126ቱ መካከልም 47 (37.3%) የሚሆኑት ሜቲሲሊን የተባለውን መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተሸከሙ ሆነዉ ተገንተዋል፡፡ ከእነዚህ 47 ህፃናት መካከል ደግሞ 32ቱ ይህን መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተቀበሉት ሆስፒታል ሲመላለሱ (ሆስፒታል ወለድ) ሲሆን ቀሪዎቹ 15 በሰፈር ውስጥ ከህብረተሰቡ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብሮች ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ፣ አብዛሃኛዎቹ ህፃናት ለዚህ መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተጋለጡት ለህክምና ክትትል ወደ ጤና ተቋማት ሲሄዱ ጤና ተቋም ውስጥ ነው የሚል ድምዳሜ ደርስናል፡፡

ስለዚህ ህብረተሰባችን ለህክምና ወደ ጤና ተቋም ሲሄድ ይዞት ከሄደው በሽታ በተጨማሪ ሌላ ይዞ እንዳይመለስ፤ ወይም ይዞት የሄደውን ጥሎ ሌላ በሽታ ይዞ ወደ ቤቱ እንዳይመለስ፤ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ጤና ባለሙያዎችም የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የአለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የእጅ አስተጣጠብ ዘዴ ተግባራዊ በማድረግ ከበሽታ አካሚና ፈዋሽ እንጅ አስተላላፊ እንዳይሆኑ በእጅጉ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ ምክራችን ነው፡፡

የዚህ ጥናት ሙሉ መረጃ ካስፈለገዎ፡ ማስፈንጠሪያዋን ይጠቀሙ፡፡
https://www.ajol.info/index.php/ejhd/article/view/178858

========================================
ተፃፈ፡ በዮሐንስ ዘነበ (ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ላቦራቶሪ ት/ት ክፍልና የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ)
========================================

Methicillin-resistant Staphylococcus aureus with genotyping method among human immunodeficiency virus positive pediatric patients in Northwest Ethiopia: A cross-sectional study design Yohannes Zenebe Martha Tibebu Begna Tulu Daniel Mekonnen Zewdie Mekonnen Abstract Abstract Background: Increasing ev...

የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ባለሞያውች ሚና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ ==================በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ ሀገራችን በማገ...
11/01/2021

የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ባለሞያውች ሚና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ
==================

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ ሀገራችን በማገልገል ላይ ያሉ የኢትዮጵያ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ሚና ላቅ ያለ ነበረ፡፡

ባለሞያዎቹ ነባር የመንግስትና የግል ከዚህ ቀደም ለሌሎች በሽታዎች (ኤች አይ ቪ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ ወባና የመሳሰሉት) የምርመራ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የሞሎኩላር ላቦራቶሪዎችን ለኮቪድ-19 ምርመራ በአዲስ መልኩ አደራጅተዋል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የሞሎኩላር ላቦራቶሮችን ለኮቪድ-19 ምርመራ አመቺ ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰርተው፣ የሚጠበቅባቸውን የቅድመ ምርመራ ልኬት አቅም ግምገማ በተሳካ ሁኔታ አልፈው የምርመራ አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ አስተወፆ አድርገዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ሰዓት 73 ላቦራቶሪዎች በሀገራችን የኮቪድ-19 ሞሎኩላር ምርመራ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ 16ቱ የግል ተቋማት ናቸው፡፡ በእነዚህም ሞሎኩላር ላቦራቶሪዎች ከ1.8 ሚሊዮን ባላይ ግለሰቦች የሞሎኩላር የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ አገልግሎታቸውንም ቀጥለዋል፡፡

በዚህም እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ድርስ 127, 227 በኮቪድ-19 የተጠቁ ግለሰቦችን መለየት ተችሏል፡፡ ይህም ከተያዙት ግለሰቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች እራሳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በማግለል የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ አግዟል፡፡ በተለይ ክትባት በሌለበት ጊዜና ክትባቱ ወደ ሀገረችን ባልገባበት ሁኔታ የላቦራቶሪ ምርመራ ለበሽታው ቁጥጥር ሚናው ከክትባት አይተናነስም፡፡

የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ባለሞያዎች 1, 836, 527 ምርመራዎችን ለማከናወን ከምርመራው ውስብስብነት፣ ውጤት ለማድረስ ከሚወስደው ጊዜ እና በሀገራችን የሞሎኩላር ላቦራቶሪዎች ቁጥር ውስንነት ምክንያት ከመንግስት የሥራ ሰዓት ውጭ (አዳርና በዓላትን ጨምሮ) ከቤተሰባቸው እራሳቸውን በማግለል ማህበረሰባቸውን በማገልገል ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፣ በመወጣት ላይም ይገኛሉ፡፡

ለዚህም አገልግሎታቸው ከአንዳንድ ሚዲያዎች የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ምስጋናን ተችሯቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሸገር 102.1 በተደጋጋሚ አየር ላይ ምስጋና ሲያስተላልፍ አድምጨዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ጣቢያው ባለሞያዎቹን የገለፀበት መንገድ ውስንነት ቢታይበትም፤ የ "ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች" በማለት ቢሆንም፡፡

የላቦራቶሪ ሞያ በኢትዮጵያ በመጀመሪያ (BSc)፣ በሁለተኛ (MSc)ና በሶስተኛ (PhD) ድግሪዎች አልፎም በሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ በሚገባ ቢገኝም የማህበረሰባችንና ማህበረሰብን ማንቃት የሚጠበቅባቸው ሚዲያዎቻችን አረዳድ ውስንነት በግልፅ የሚታይ ነው፡፡

የ "ላቦራቶሪ ቴክኒሻን" በዲፕሎማ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ብቻ የሚገልፅ ስያሜ መሆኑን ያለመረዳት ይታያል፡፡ ነገር ግን በሀገራች የኮቪድ-19 ምርመራን በማሳለጥ ሚናቸውን የተወጡ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ደረጃ ግን ከላይ አንደገለፅኩት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና ስፔሻሊቲዎች የሚገኙትንም ያካትታል፡፡

ሆኖም በሸገር 102.1 በተደጋጋሚ ሲደረግልን የነበረውን ምስጋና ሙሉ በሙሉ ከልብ ተቀብለናል፡፡ እናመሰግናለን!

አበባው ከበደ (ከኢ.ህ.ጤ.ኢ)

SHEGER FM 102.1 RADIO
Lia Tadesse, Minister of Health

የኮሮና ቫይረስ ዋና ፕሮቲየዝ ኢንዛይምና እና የመድሃኒት ኢላማነቱ(SARS-CoV-2 main protease as a drug target)====================================...
11/01/2021

የኮሮና ቫይረስ ዋና ፕሮቲየዝ ኢንዛይምና እና የመድሃኒት ኢላማነቱ
(SARS-CoV-2 main protease as a drug target)
=========================================

ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 በተባለዉ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የሚመጣዉ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጠጠረ ክንዱን በዓለም ላይ ማሳረፍ ከጀመረ እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ሞላዉ፡፡ በብዙ መንገድ መተላለፍ መቻሉ እና ፍቱን ክትባትም ሆነ መድሃኒት ባለመገኘቱ ምክንያት ከ86 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ታመዋል፣ ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ህይወታቸዉን አጥተዋል፣ አለም ክፉኛ ጠላት ገጥሟት ባጅቷል፡፡ ያስከተለው ቀውስ የጤና ብቻ አይደለም፣ ዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀዉስም ጭምር እንጅ!!፡፡

የቫይረሱ ዘረ መል እንዲራባ እና ሙሉ ቫይረስ ሆኖ ሌሎች ህዋሳትን እንዲያጠቃ ከሚያደርጉ ወሳኝ የቫይረሱ አካላት መካከል ዋና ፕሮቲየዝ (main protease) የተሰኘዉ ኢንዛይም የአንበሳዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ኢንዛይም የቫይረሱ አካላት ተሰርተዉ ካለቁ በኋላ ወደ ንዑስ አካላት እንዲቆራረጡ በማድረግ በሽታ አምጪዉ ሙሉ ቫይረስ (virion) እንዲፈጠር በማድረግ በቫይረሱ የህይወት ዑደት ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ማሽን ነው (ምስል 1) ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሳይንቲስቶች ይህን ወሳኝ ማሽን የሆነ ኢንዛይም የሚገታ መድሃኒት በማፈላለግ ላይ ሲገኙ ብዙ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶችም በመመዝገብ ላይ ናቸዉ፡፡

ይህ ኢንዛይም የተመራማሪዎችን ትኩረት የሳበበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ

1️⃣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ቫይረሶችን ማለትም ኤች አይ ቪ እና ሄፕታይትስ ሲን ለማከም የዚህን ኢንዛይም ተግባር የሚገቱ መድሃኒቶች ተሰርተዉ ዉጤታማ በመሆናቸዉ

2️⃣ ኢንዛይሙ ከሌሎች ፕሮቲኖች አንፃር ሲታይ የዘረ መል ለዉጥ የማድረግ ታሪኩ በጣም አነስተኛ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ የሳርስ ኮሮናቫይረስ-2 ዋና ፐሮቲየዝ ዘረ መል ከሳርስ ኮሮና ቫይረስ-1 እና መርስ ኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ኢንዛይሞች ጋር ሲነፃፀር የኢንዘይሙ ገባሪ አካል (active site) መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ተመሳሳይ የዘረ መል ዉቅር (DNA sequence) አለዉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ በሽታዎችን መግታት የሚችሉ (broad-spectrum) መድሃኒቶችን ለመስራት ያስችላል፡፡

3️⃣ ኢንዛይሙ የተሻሻለ ክወና (enhanced catalytic activity) በማሳየቱ መድሃኒቶች በቀላሉ እንዲያጠቁት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡

4️⃣ ከዚህ ኢንዛይም ጋር ተመሳሳይ ተግባር ያላቸዉ ኢንዛይሞች በሰዉ ህዋሳት ዉስጥ ስለሌሉ፤ ለዚህ ኢንዛይም መምቻ ተብለው የሚሰሩ መድሃኒቶች ከኢላማ ዉጪ (off-target) የማጥቃት እድላቸዉ ይቀንሳል፡፡ ይህም ይህን ኢንዛይም ኢላማ አድርገው የሚሰሩ መድኃኒቶች አነስተኛ መርዛማነት (low toxicity) ያላቸዉ መድኃኒቶች እንድሆኑ ያደርጋል፡፡

5️⃣ ከዚህ ባሻገር ኢንዛይሙን የሚመቱ መድሃኒቶች የሚጣበቁበት ቦታ ምቹ የሆነ መዋቅር እና ቅርፅ (structure and shape) ስላለዉ የመድሃኒቶችን ፍቱንነት ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል (ምስል 2ን ይመልከቱ)፡፡

በአሁኑ ሰዓት የኢንዛይሙን መዋቅር መሰረት ያደረጉ ብዙ የመድሃኒት ምርምሮች በኮምፒዉተር ስሌት፣ በህዋስ ምርመራ (cell culture) እና በክሊኒካዊ ሙከራ (clinical trial) ደረጀ እየተካሄዱ ሲሆን ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ዉጤቶች እየታዩ ነዉ፡፡ ለምሳሌ 11u, 11r, 13a, 13b, N3, 11a, 11b (ምስል 3) የሚባሉ አዳዲስ መድሃኒቶች በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለሄፕታይቲስ ሲ እና ለኤች አይ ቪ የሚሰጡ መድሃኒቶች እና ከእፅዋት የሚገኙ ባህላዊ ቅመሞች የዚህን ኢንዛይም ተግባር በማስተጓጎል ደረጃ የተሻሉ መሆናቸው ምናልባትም በቅርብ ቀን በሽታዉን የሚገታ መድሃኒት ሊኖር እንደሚችል አመላካች ነዉ፡፡

ይሁን እንጅ በሙከራ ላይ የሚገኙ ብዙ መድሃኒቶች ያሉበት የመድሃኒት ቅመማ ደረጃ ገና እንጭጭ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሰዉ ህዋሳት ዉስጥ ምን ያህል ዉጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች የቫይረሱ ክፍሎች ላይ የሚደረጉ የዘረ መል ለዉጦች የዚህን ኢንዛይም መዋቅር ይብዛም ይነስም መለወጥ መቻላቸዉ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም እጩ መድሃኒቶች ሲዘጋጁና ምርምሮች ሲካሄዱ ይህን ጉዳይ ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው፡፡ይህን መሰል ምርምሮች ሲደረጉ የተላያዩ የሙያ ዘርፎች ቢካተቱ ጠቀሜታው የላቀ ስለሚሆን ታሳቢ እንዲደረግ አንመክራለን፡፡

--------------------------------------------------------------------------
ተፃፈ፡ በኃይለማርያም ምህረቴ (ከደብረ ማርቆስ የኒቨረሲቲ፣ በቻይና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪና ሞለኪዩላር ባዮሎጂ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ)
--------------------------------------------------------------------------

ለበለጠ መረጃ
1. Zhang, L., Lin, D., Sun, X., Curth, U., Drosten, C., Sauerhering, L., . . . Hilgenfeld, R. (2020). Crystal structure of SARS-CoV-2 main protease provides a basis for design of improved α-ketoamide inhibitors. Science, 368(6489), 409-412.
2. Mengist, H. M., Fan, X., & Jin, T. (2020). Designing of improved drugs for COVID-19: Crystal structure of SARS-CoV-2 main protease M pro. Signal Transduction and Targeted Therapy, 5(1), 1-2.
3. Dai, W., Zhang, B., Jiang, X.-M., Su, H., Li, J., Zhao, Y., . . . Liu, F. (2020). Structure-based design of antiviral drug candidates targeting the SARS-CoV-2 main protease. Science, 368(6497), 1331-1335.
4. Ullrich S, Nitsche C. The SARS-CoV-2 main protease as drug target. Bioorg Med Chem Lett. 2020 Sep 1;30(17):127377. doi: 10.1016/j.bmcl.2020.127377. Epub 2020 Jul 2. PMID: 32738988; PMCID: PMC7331567

11/01/2021

ማይክሮፕላስቲክ
========
ማይክሮፕላቲኮች በትንሹ ተቆራርጠው እና ተበታትነው የሚገኙ ፕላስቲኮች ማለት ነው፡፡ ከትንሽነታቸውም የተነሳ በአየር ላይ ሊንሳፈፉ እና ወደ ሰው መተንፈሻ አካል ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከዛም አልፈው በሳንባ እና በአንጀት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ መጠናቸውን በልኬት ለማስቀመጥ ያህል ከ5 ሚሊሜትር ያነሱ እና በዓይን እስከማይታዩ ድረስ ትንሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማይክሮፕላስቲኮች በኢንደስትሪዎች ውስጥ ለተለያየ ጥቅም ሲባል ሊፈበረኩ ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም ከተሰባበረ እና ከተቆራረጠ ፕላስቲክ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
በተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ ማይክሮፕላስቲኮች የሰው ልጅ ዓይነምድር ውስጥ እየተገኙ እንደሆነ ተጨባጭ ማስረጃዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው በሰው ልጅ አፍ በኩል ገብተው፣ በአንጀት ውስጥ አልፈው እንደሚወጡ ነው፡፡ ስለዚህ ከምግብ ማንሸራሸሪያ አካላት ወይም ከአንጀት እና ሆድ ዕቃ ጋር ተያያዥ የጤና ዕክል ላለባቸው ሰዎች የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚያመጣው የጤና ዕክል መጠን ስለማይታወቅ፤ ለቀጣይ ጊዜያት ምን ያህል ጉዳት ማድረስ እንደሚችል እና መፍትሄው ላይ ብዙ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላኛው የማይክሮፕላስቲኮች በጨው ውስጥ መገኘት ነው፡፡ ምክንያቱም ጨው የሚገኘው ከባህር እና ከውሃ አካላት እንደመሆኑ እና የውሃ አካላትም በፕላስቲክ ቆሻሻዎች እየተበከሉ ያሉ በመኖራቸው ነው፡፡

ስለዚህ በጤና ላይ የሚያደርሱትን ዕክሎች በጥናት ታውቆ እስኪረጋገጥ ድረስ መፍትሔው ላይ ማተኮር ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ በቤታችን፣ በዙሪያችን እና በአካባቢያችን የሚገኝ ማንኛውንም ዓይነት ፕላስቲኮች ሳይቆራረጡ እና ሳይሰባበሩ በተገቢው ሁኔታ ማስወገድ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ተፃፈ፡
በ Alula (Anley) Teferra (Ph.D. candidate)
Microbiology (Cell), Pukyong National University, Korea
(27/04/2013 ዓ.ም)

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Ethio-Lab Page posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share

Share on Facebook Share on Twitter Share on LinkedIn
Share on Pinterest Share on Reddit Share via Email
Share on WhatsApp Share on Instagram Share on Telegram

Category