8896 Hello Doctor Ethiopia

8896 Hello Doctor Ethiopia Did you know that you can call "8896" to get 24/7 access to a medical doctor who will consult with you on any health issue for only 6 birr/min?

helloDoctor®, allows you to call at any time and from anywhere in Ethiopia and get instant access to valuable health information, tools for managing your health, and support to those who seek information.

ዉድ የሃሎ ዶክተር ደንበኞቻችንእንኳን ለ2014 ዓ.ም አደረሳችሁ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር እንዲሆንልዎ 8896 ሃሎ ዶክተር ይመኝልዎታል፤የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር ...
10/09/2021

ዉድ የሃሎ ዶክተር ደንበኞቻችን
እንኳን ለ2014 ዓ.ም አደረሳችሁ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር እንዲሆንልዎ 8896 ሃሎ ዶክተር ይመኝልዎታል፤የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር ራስዎንና አካበቢዎን ይጠብቁ፡፡

መልካም አዲስ አመት!

ቃር (Heartburn) ሊያስነሱ/ሊባብሱ የሚችሉ ነገሮችየተከበራችሁ የ8896 ሄሎ ዶክተር ወዳጆቻችን፤ እስቲ ዛሬ ቃርን ሊባብሱ ስለሚችሉ ነገሮች ጥቂት ምክር እንለግሳችሁ።ምግብ አብዝቶ መመገ...
02/09/2021

ቃር (Heartburn) ሊያስነሱ/ሊባብሱ የሚችሉ ነገሮች

የተከበራችሁ የ8896 ሄሎ ዶክተር ወዳጆቻችን፤ እስቲ ዛሬ ቃርን ሊባብሱ ስለሚችሉ ነገሮች ጥቂት ምክር እንለግሳችሁ።

ምግብ አብዝቶ መመገብ፡-
በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ሰዉ በምንም ያህል ጊዜ ልዩነት ይሁን ወይም ምንም አይነት የምግብ አይነት ይመገብ፣ ከመጠን ያለፈ አመጋገብ/ አብዝቶ ከተመገበ ለቃር ሊዳርገዉ ይችላል፡፡ ስለሆነም መጥኖ መመገብ ከምግብ መጠን ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ቃር ሊከላከልልዎ ይችላል፡፡

በፍጥነት መመገብ፡-
የስነምግብ ባለሙያዎች እንደእንደሚሉት ምግብን በችኮላ/በፍጥነት መመገብ ለቃር ተጋላጭነትዎን ይጨምራል፡፡ ስለሆነም ምግብ በሚመገቡበት ወቅት በእርጋታ ቢሆን ይመረጣል፡፡

ስብነት ያላቸዉ ምግቦች
ስብነት የበዛባቸዉ ምግቦች በጨጓራችን ዉስጥ ለመፈጨት ረዘም ያሉ ሰዓታትን ይወስዳሉ፡፡ ምግብ በጨጓራችን ዉስጥ ለመፈጨት ረዘም ያለ ሰዓታት በወሰደ ቁጥር ደግሞ ለቃር ተጋላጭነታችንን ይጨምራል፡፡ የዚህን ተጋላጭነት ከሚጨምሩ ነገሮች ዉስጥ አንዱ ደግሞ ስብነት ያላቸዉን ምግቦችን አብዝቶ/ ከመጠን አሳልፎ መመገብ ነዉ፡፡

አሲድነት ያላቸዉ ምግቦች
እንደ ቲማቲም፣ ፍራፍሬዎች (ብርቱካን፣ ወይን፣ ሎሚ፣ ኮምጣጤ) ያሉ ምግቦች በራሳቸዉ ወይም በባዶ ሆድዎ ቢመገቧቸዉ ቃርን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

ፈሳሾች/መጠጦች፡-
ለቃር ሊያጋልጥዎ የሚችሉት ምግቦች ብቻ አይደሉም፡፡ ፈሳሾችም ቃርን በቀላሉ ሊያስነሱብዎ ይችላሉ፡፡ እንደ ቡና፣ ካፊን ያለበት ሻይ፣ አልኮሆልና ጋዝ ያላቸዉ/ካርቦኔትድ መጠጦች ለቃር ተጋላጭነትዎን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ ቡና ጨጓራዎ ብዙ አሲድ እንዲያመነጭ ያደርጋል፤ አልኮሆል ደግሞ የታችኛዉ የጎሮሮ መቋጠሪያ/መዝግያ እንዲላላ በማድረግ የጨጓራ ይዘቶች ወደ ጉሮሮ እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡ ጋዝ ያላቸዉ መጠጦች በዉስጣቸዉ ካፊን ሊኖራቸዉ ይችላል፡፡ ነገር ግን ካፊን ባይኖራቸዉም ጨጓራዎ እንዲነፋ ስለሚያደርጉ ለቃር ሊያጋልጥዎ ይችላሉ፡፡ ካፊንና ጋዝ የሌለባቸዉ መጠጦች ቃርን የማስከተል አቅማቸዉ በጣም አነስተኛ ነዉ፡፡ ስለሆነም ካፊን የሌለዉ ኸርባል ሻይ፣ ወተት፣ እና ዉሃ ቃርን ለመቀነስ የሚመረጡ የፈሳሽ አይነቶች ናቸዉ፡፡

ቾኮሌት
ቾኮሌቶች በዉስጣቸዉ ስብና ካፊን ሊኖራቸዉ ስለሚችል ለቃር ችግር ሊያጋልጡዎት ይችላሉ፡፡ “ኸረ! ተገኝቶ ነው?!” የሚሉም አይጠፉም፡፡ ከተገኘ እሰየው፥ ነገር ግን መጥኖ መመገብ ተገቢ ነው። በተጨማሪም ቾኮሌቶችን ከበድ ያለ ምግብ ከተመገቡ በኃላና በባዶ ሆድዎ መመገብ የለብዎም፡፡

ቃርን ለመቀነስ የሚመከሩ
• ማስቲካ ማኘክ፡- ማስቲካ ሲጠቀሙ ምራቅ ብዙ ስለሚመርቱ ይህ አሲዱን ለማክሸፍ/ለመቀነስ ይረዳዎታል፡፡ ቀረፋ ወይም ፔፐርሜንት/ሜንት ማስቲካዎችን መጠቀም የለብዎም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ማስቲካዎች የታችኛዉ የጉሮሮ መቋጠሪያ/መዝግያ ስለሚያላሉ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

ሌሎች ቃርን ለመቀነስ የሚረዱ ነገሮች
• እራትዎን ከመኝታ ሰዓትዎ ከ3 ሰዓታት በፊት አስቀድመዉ መመገብ
• ከፍ ያለ ትራስ መጠቀም
• ምግብ ከተመገቡ በኃላ ተንጋለዉ ያለመተኛት
• ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቆም
• ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል

የቃር አልፎ አልፎ መከሰት የተለመደና ብዙም ሊያሳስብዎ የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ቃር በተደጋጋሚ እየመጣ/እየተከሰተ ካስቸገረዎ እንደ ጋስትሮኢሶፋጂያል ሪፍለክስ ዲዚዝ/ Gastroesophageal Reflux Disease (GERD) ያሉ ህመሞች ምልክት ሊሆን ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ይጠበቅብዎታል፡፡

ያለ መድሃኒት የታችኛዉ የጀርባ ህመምን ለማቃለል/ለማከም የሚረዱ 4 መንገዶችእንደ የአሜሪካ ናሽናል የጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ከ10 ሰዎች ዉስጥ 8ቱ በህይወታቸዉ ዘመን የሆነ ጊዜ የጀርባ ህመ...
19/08/2021

ያለ መድሃኒት የታችኛዉ የጀርባ ህመምን ለማቃለል/ለማከም የሚረዱ 4 መንገዶች

እንደ የአሜሪካ ናሽናል የጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ከ10 ሰዎች ዉስጥ 8ቱ በህይወታቸዉ ዘመን የሆነ ጊዜ የጀርባ ህመም ሊያማቸዉ እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ እንክብሎችን መዉሰድ ለጊዜዉ ህመምዎን ሊያስታግስ ቢችልም ዘላቂነት ያለዉ የጀርባ ጤንነት እንዲኖርዎ የሚከተሉትን ምክሮች /ነገሮች ሊተገብሩ ይችላሉ፡፡

1. ዮጋ፡- ዮጋ በመስራትና የጀርባ ህመምዎን መቀነስ ይቻል፡፡

2. ማሳጅ፡- መጨናነቅ የጀርባ ህመም እንዲመጣ የሚያደርግ ሲሆን ይህን ለመቀነስ ማሳጅ ማድረግ ይመከራል

3. የደረቅ መርፌ ህክምና፡- መርፌዉ ሊያስፈራዎ አይገባም፡፡ይህ የቻይና የደረቅ መርፌ ህክምና ዘመናትን የተሸገረ ሲሆን መርፌዉን በተወሰነ የሰዉነት ክፍል በመዉጋት የሚሰራ ነዉ፡፡በጥናቶች እንደተረጋገጠዉ ይህ የህክምና አይነት እንደ ዘመናዊ የህመም ማስታገሻ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከህመሙ የመፈወስ ብቃት አለዉ፡፡

4. ወክ ማድረግ፡- አንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ወደጀርባ አጥንትዎ ዲስክ የሚሄደዉን የደም ዝዉዉር ስለሚቀንስ መጨናነቅን ያመጣል፡፡ስለሆነም ህመሙን ለመቀነስ በየቀኑ ወክ ማድረግ ይመከራል፡፡ለረጅም ሰዓት የሚቀመጡ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከተቀመጡበት ቦታ እየተነሱ መንቀሳቀስ ህመምዎን ለመቀነስ ይረዳዎታል፡፡

እከክ (Scabies)እከክ ቆዳን የሚያሳክክ በቆዳ ስር በሚቀመጡ ሳርኮፕቴስ እስኬቢስ በሚባሉ ተዋሲያን የሚከሰት የቆዳ ላይ ችግር ነዉ፡፡ ህመሙ በቤተሰብ፣ በህፃናት እንክብካቤ ማዕከል፣ ትምህ...
10/08/2021

እከክ (Scabies)

እከክ ቆዳን የሚያሳክክ በቆዳ ስር በሚቀመጡ ሳርኮፕቴስ እስኬቢስ በሚባሉ ተዋሲያን የሚከሰት የቆዳ ላይ ችግር ነዉ፡፡ ህመሙ በቤተሰብ፣ በህፃናት እንክብካቤ ማዕከል፣ ትምህርት ቤቶች፣የህመሙማን መንከባከቢያ ማዕከልና እስር ቤቶች ዉስጥ በቀላሉ በአካላዊ ንክኪ ሊተላለፍ የሚችል የህመም አይነት ነዉ፡፡

በቆዳዎ ላይ ሊቀቡ የሚችሉ ምድሃኒቶች በሽታዉን ሊያመጡ የሚችሉ ተዋሲያንንና እንቁላላቸዉን በቀላሉ የሚገድል ነዉ፡፡

የህመሙ ምልክቶች፡-
· የቆዳ ማሳከክ፡- ብዙዉን ጊዜ ከፍ ያለና ማታ ማታ የሚባባስ
· ቀጫጭን የሆኑ የተቦረቦሩ የቆዳ ላይ ቁስለቶች መታየት
የተቦረቦሩ ቁስለቶች በተጣጠፉ የቆዳ ክፍሎች ላይ በብዛት ይታያል፡፡ እከክ ምንም እንኳ በየትኛዉም የሰዉነት ቆዳ ላይ ቢከሰትም በተለይ በሚከተሉት የሰዉነት ክፍሎች አካባቢ በብዛት ይከሰታል፡-

· በጣቶች መካከል
· በብብት ስር
· በወገብ አካባቢ
· በዉስጠኛዉ የእጅዎ ክፍል
· በዉስጠኛዉ የክርን ክፍል
· በዉስጥ እግር
· ጡት አካባቢ
· በወንዶች ብልት አካባቢ
· በመቀመጫ አካባቢ
· በጉልበት አካባቢ ናቸዉ፡፡

ከዚህ በፊት በእከክ ተይዘዉ ከነበረ አሁን በድጋሚ ቢያዙ የህመሙ ምልክቶች በጥቂት ቀናት ዉስጥ የሚታይ ሲሆን ከዚህ በፊት በእከክ ተይዘዉ የማያዉቁ ከሆነ ግን የህመሙ ምልክቶች ለመታየት እስከ 6 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ ማስታወስ የሚገባዎ ነገር ቢኖር ምንም እንኳ የህመሙ ምልክት ባይታይቦትም በሽታዉን ሊያሰራጩ እንደሚችሉ ነዉ፡፡ ቅርበት ያለዉ አካላዊ ግንኙነትና ልብስን ወይም መኝታን መጋራት ለህመሙ መዛመት/መተላለፍ ዋነኛዉ መንገድ ነዉ፡፡

ሊደረግ የሚችል ህክምና
የእከክ ህክምና የበሽታዉን አምጭ ተዋሲያን ማጥፋት ሲሆን በክሬምና በሎሽን መልክ ያሉ መድሃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡እከክ በቀላሉ የሚተላለፍ የቆዳ ላይ ችግር ስለሆነ ሌሎች የቤተሰብ አባላት የህመሙ ምልክቶች ባይኖራቸዉም የህክምና ባለሙያዎ መድሃኒቱን ለሁሉም የቤተሰብ አባላትዎ ሊያዝ ይችላል፡፡

እንዴት መከላከል ይቻላል?
ህመሙ ተመልሶ እንዳይዞትና ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይተላለፍ ሁሉንም ልብሶችዎንና አንሶላዎችን በንፅህና ማፅዳት፡፡ ይህም በሞቀ ዉሃና ሳሙና ልብሶችን፣ ፎጣዎችንና አንሶላዎችን ህክምና ከመጀመርዎ ከሶስት ቀናት በፊት የተጠቀሙባቸዉን በሙል በደንብ ካጠቡ በኃላ በሙቀት ማድረቅ፡፡ በዉሃ መታጠብ የማይችሉትን ደግሞ በፀሃይ ብርሃን ማድረቅ/ማሞቅ ናቸዉ፡፡

የሰዉነት ጠረንን ለመቀነስ የሚመከሩ ምክሮችየሰዉነቴ ጠረን ተለወጠ/ሰዉነቴ ጠረን አመጣ ብለሁ አስበሁ/ተጨንቀዉ ይሆናል፡፡ ይህ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰዉነትዎ ጠረን እንዲቀንስ/እን...
05/07/2021

የሰዉነት ጠረንን ለመቀነስ የሚመከሩ ምክሮች

የሰዉነቴ ጠረን ተለወጠ/ሰዉነቴ ጠረን አመጣ ብለሁ አስበሁ/ተጨንቀዉ ይሆናል፡፡ ይህ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰዉነትዎ ጠረን እንዲቀንስ/እንዲጠፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚከተሉትን 6 ምክሮች ይሞክሩዋቸዉ፡፡

1. ንፅህናዎን በደንብ አድርገዉ መጠበቅ፡- ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ሻወር በመዉሰድ የሰዉነት ላብንና በቆዳዎ ላይ ያሉ ባክቴሪያዎችን መቀነስ ይችላሉ (የቆዳ ድርቀት የሚያስቸግርዎ ከሆነ ወይም የቆዳ ችግር ካለዎ ቆዳዎ የበለጠ ለድርቀት እንዳይጋለጥ ሻወር በየቀኑ መዉሰድ አይመከርም)፡፡ ላብ በራሱ ሽታ የለዉም፡፡ ነገር ግን በቆዳችን ላይ የሚኖሩ ባክቴሪያዎች ከላብ ጋር በሚደባለቁበት ወቅት በፍጥነት ስለሚራቡ ላብ ጠረን እንዲያመጣ ያደርጉታል፡፡ ስለሆነም በተለይ ላብ በብዛት የሚያጠቃቸዉ ቦታዎችን በደንብ መታጠብ የሰዉነት ጠረንን ይቀንሳል፡፡ ላብ በጣም ከሚያልባቸዉ ሰዎች ይልቅ መጠነኛ ላብ የሚያልባቸዉ ሰዎች የሰዉነት ጠረን መለወጥ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ምክንያቱም ላብ በብዛት የሚያልባቸዉ ሰዎች ጠረንን ሊለዉጡ/ሊያመጡ የሚችሉ ባክቴሪያዎች በላብ ስለሚታጠቡ ነዉ፡፡

2. ባክቴሪያን መቀነስ የሚችሉ/ አንቲማይከሮቢያል ሳሙናዎችን መጠቀም፡- ሰዉነትዎን በሚታጠቡበት ወቅት ባክቴሪያን ሊያስወግዱ/ሊቀንሱ የሚችሉ ሳሙናዎችን መጠቀም፡፡ ይህን ማድረግ በሰዉነትዎ ላይ ያሉ ባክቴሪያዎችን መጠን ስለሚቀንሱ የሰዉነትዎን ጠረን ለመቀነስ ይረዳዎታል፡፡ ስለሆነም የሰዉነት ጠረን የሚያስቸግርዎ ከሆነ የገላ ሳሙና ሲገዙ ‘‘አንቲባክቴሪያል '' የሚል በሳሙናዉ መያዣ ላይ እንዳለ አይተዉ መሞከር ይችላሉ፡፡

3. ሻወር ከወሰዱ በኃላ ሰዉነትን በፎጣ በደንብ አድርጎ ማደራረቅ፡- ሰዉነትዎን ከታጠቡ በኃላ መላ ሰዉነትዎን በፎጣ በደንብ አድርገሁ ማደራረቅ፡፡ በተለይ ላብ በብዛት በሚያልብዎ ቦታዎች ላይ በደንብ መድረቁን ማረጋገጥ፡፡ ቆዳዎ በደንብ ከደረቀ የሰዉነትን ጠረን ሊለዉጡ የሚችሉ ባክቴሪያዎች በቀላሉ በቆዳዎ ላይ ማደግ አይችሉም፡፡

4. ዶድራንቶችን ወይም የላብ መቀነሻዎችን መጠቀም፡- ሰዉነትዎን ከታጠቡና በደንብ ካደራረቁ በኃላ ዶድራንቶችን ወይም ላብ የሚቀንሱ ዶድራንቶችን በብብትዎ ስር መጠቀም፡፡ዶድራንቶች ላብን ባይከላከሉም በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጡትን/የሚከሰቱትን መጥፎ ሽታዎች ይቀንሳሉ፡፡

የላብ መቀነሻዎች በዉስጣቸው አልሙኒየም ክሎራይድ ያላቸዉ ሲሆን ላብንና መጥፎ የሰዉነት ጠረን ለመቀነስ ያገለግላሉ፡፡ የሰዉነት ጠረን የሚያስቸግርዎ ከሆነ ጠንከር ያሉ ዲዎድራንቶችን ያለ ትዕዛዝ ሊገዙ የሚችሉ ሲሆን በሚገዙበት ወቅት ‘‘ከፍ ያለ ጥንካሬ ያለዉ'' (higher strength due to ingredients) የሚል ፅሁፍ መዕቃዉ ላይ መኖሩን አይተሁ መግዛትና መሞከር ይችላሉ፡፡

5. የሚለብሱትን አልባሳት ንፅህና በደንብ መጠበቅ፡- በጣም የሚያልብዎ ከሆነ የሚለሱትን አልባሳት ቶሎ ቶሎ መቀያየር፡፡ አዳዲስ ልብሶች ( የታጠቡ) የሰዉነትዎን ጠረን ለመቀነስ ይረዱዎታል፡፡ የእግር ሽታ የሚያስቸግርዎ ከሆነም ካልሲዎንም ቶሎ ቶሎ መቀያየር ያስፈልጋል፡፡ የእግር ሽታን ለመቀነስ ዱቄት (ፓዉደር) ዲዎድራንቶችን በጫማዎ ዉስጥ መጠቀም፤የጫማዎን ሶል ቶሎ ቶሎ መቀያየርና ከቻሉ እግርዎን ለማናፈስ ባዶ እግር መሆን ይመከራሉ (ለምሳሌ በቤት ዉስጥ ሁሌ በነጠላ ጫማ/ ባዶ እግር መሆን)፡፡

6. ለሰዉነት ጠረን መለወጥ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችንና መጠቶችን መቀነስ ወይም መተዉ፡- የሰዉነትዎን ላብ ሊጨምሩ የሚችሉ ምግቦች እንደ ቃሪያ ወይም ቅመማ ቅመም ያላቸዉ ምግቦች ለሰዉነት ጠረን መለወጥ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሽንኩርት ወይም ነጭ ሽንኩርት ከተመገቡ ሽታቸዉ ከላብ ጋር ሊወጣ ስለሚችል መጥፎ ጠረን እንዲኖርዎ ያደርጋሉ፡፡ በዉስጣቸዉ ካፊን ያላቸዉ ነገሮች እንዲሁም አልኮሆል (መጠጥ) ሰዉነትዎን ብዙ እንዲያልብዎት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ደም መለገስ( Blood Donation)ደም መለገስ በፍላጎት/በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ በጎ ተግባር ነዉ፡፡ እርስዎ ደም ለመስጠት ተስማምተሁ ከለገሱ በኃላ ደሙ ለሌላ የሰዉ ደም ለሚ...
14/06/2021

ደም መለገስ( Blood Donation)

ደም መለገስ በፍላጎት/በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ በጎ ተግባር ነዉ፡፡ እርስዎ ደም ለመስጠት ተስማምተሁ ከለገሱ በኃላ ደሙ ለሌላ የሰዉ ደም ለሚያስፈልገዉ ግለሰብ ይለገሳል፡፡ በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሌላ ሰዉ ደም ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ በቀዶ ጥገና ጊዜ የሚፈልጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከአደጋ በኃላ ወይም የዉስጥ ደዌ ችግር ኖሮዋቸዉ ደም ወይም የተወሰኑ የደም ሴሎችን በሚፈልጉበት ወቅት ነዉ፡፡ ስለሆነም ደም መለገስ እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች ይፈታል፡፡

በጣም የተለያዩ የደም መለገስ አይነቶች አሉ፡፡እነርሱም

• ሙሉ ደም(Whole blood)፡- ይህ ብዙዉን ጊዜ የተለመደዉ አይነት ሲሆን ሁሉንም አይነት የደም ሴሎች አንድ ላይ የሚለግሱበት ዘዴ ነዉ፡፡ ከዚያን በኃላ ደሙ ወደ ተለያዩ የደም ክፍሎች እንዲለያይ ይደረጋል (ቀይ የደም ሴሎች፣ፕላዝማና ፕላትሌትስ)
• ፕላትሌትስ፡-ይህ አይነቱ የመለገስ ሂደት አፌሬሲስ(apheresis) የሚባል ሲሆን ደም የሚለግሰዉ ግለሰብ ከደሙ ውስጥ ፕላትሌትስንና የተወሰነ ፕላዝማን ለይቶ መዉሰድ የሚችል ማሽን ላይ ይደረግና ቀሪዉን ወደ ለጋሹ እንዲመለስ የሚያደርግ ሂደት ነዉ፡፡
• ፕላዝማ፡-ፕላዝማ በአፌሬሲስ ሂደት ወቅት ከፕላትሌትስ ጋር ወይም ብቻዉን ከለጋሹ የሚወሰድ ነዉ፡፡
• ቀይ የደም ሴሎች (ደብል ሬድ ብለድ ሴል)፡-ቀይ የደም ሴሎች አንደ ፕላትሌትስና ፕላዝማ በፌሬሲስ መንገድ ከደም ለጋሹ ሊሰበሰብ ይችላል፡፡

የደም መለገስ የሚመጣዉ ችግር አለ(Risks)?
ደም መለገስ የሚያመጣዉ ምንም ችግር የለም!!! ለያንዳንዱ ለጋሽ አዲስና ጤንነቱ የተጠበቀ ዕቃዎች ስለሚጠቀሙ ደም በመለገስዎ በደምና በደም ንኪኪ ሊተላለፉ የሚችሉ ኢንፌክሽኖች ሊይዝዎ አይችሉም፡፡
እርስዎ ጤናማ ከሆኑ ጤንነትዎ ላይ ምንም አይነት አደጋ/ችግር ሳይከተል ደም መለገስ ይችላሉ፡፡ ደም በለገሱ በ24 ሰዓታት ዉስጥ ሰዉነትዎ ደም በመለገስ ወቅት ያጣዉን የፈሳሽ መጠን የሚተካ ሲሆን በተወሰኑ ሳምንታት ዉስጥ ደግሞ ሰዉነትዎ በደም መለገስ ወቅት ያጣዉን ቀይ የደም ሴሎችን ሙሉ በሙሉ ይተካል፡፡

ደም ለመለገስ የሚደረጉ ዝግጅቶች
ሙሉ ደምም ይሁን ፕላዝማና ፕላትሌትስ ከመለገስዎ በፊት ሊሟሉ የሚገባቸዉ ነገሮች፡-
• ሙሉ ጤነኛ መሆን
• ቢያንስ 18 አመትና ከዚያን በላይ መሆን፡-ደም ለመለገስ መነሻ ዕድሜ ከሀገር ሀገር የሚለያይ ሲሆን የላይኛዉ እድሜ ጣሪያ ግን ገደብ የለዉም፡፡
• ክብደትዎ ቢያንስ 45 ኪሎግራም መሆን፡፡
• አካላዊና ሌሎች የጤና ምርመራ ማለፍ የሚችል መሆን አለበት፡፡
የሰዉነት ቀጭንና ወፍራም መሆን ደም ለመስጠት/ለመለገስም ሆነ ላለመለገስ እንደ ቅድመ ሁኔታ አያገለግልም፡፡ ይልቁንም ከላይ የተዘረዘሩትን ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟሉ ከሆነ ሰዉነትዎ ቀጭን ቢሆኑም እንኳ መለገስ ይችላሉ፡፡

ሌላዉ የተወሰኑ ሰዎች ከደም መለገስ ጋር ተያይዞ ያልተገባ ግንዛቤ ያላቸዉ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ ደም መለገስ ጉዳት እንዳለዉና የሰዉ ደም እንደሚሸጥ ይገኙበታል፡፡በመሰረቱ የሰዉ ደም ተሸጦ አያዉቅም፣ሊሸጥም አይችልም፡፡የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ደም ሸጦም አያዉቅም፤ወደፊትም ሊሸጥ አይችልም፡፡ ነገር ግን አላስፈላጊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ለሰዉ ሊሰጥ የሚችለዉን ደም በሚገባ ክምችቱን በደም ባንክ ዉስጥ በሚገባ እንዲጨምርና ደም በተፈለገበት ወቅት ለተጠቃሚዉ ለመለገስና እንዲሁም እጥረቱን ለማስወገድ ሁላችንንም በተቻለን መጠን ደም መለገስ ይጠበቅብናል፡፡ይህንንም አንድ ጊዜ ብቻ በዘመቻ የምናካሄደው ጉዳይ ሳይሆን ደም መለገስን እንደባህል አድርገነዉ ቢያንስ በአመት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ደም መለገስ ያስፈልጋል፡፡

ደም ለመለገስ ካሰቡበት ቀን በፊት ባለዉ ምሽት በቂ እንቅልፍ ማግኘት የሚያስፈልግ ሲሆን ከመለገስዎ በፊት ጥናማ ምግብ መመገብ፤ ስብነት ያለቸዉን( ለምሳሌ የአሳማ ስጋ)ና እንደ አይስ ክሬም ያሉ ምግቦችን ያለመመገብ፤ እስከ 473 ሚሊ ሊትር የሚደርስ ተጨማሪ ፈሳሽ ከመለገስዎ በፊት መጠጣት መቻልና ፕላትሌትስ የሚለግሱ ከሆነ ከመለገስዎ ከሁለት ቀናት በፊት ጀምሮ አስፒሪን ያለመዉሰድ ይመከራሉ፡፡

በተጨማሪም ደም ከመለገስዎ በፊት ሚስጥርነቱ የተጠበቀ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በደምና የደም ዉጤት በሆኑ ነገሮች ሊተላለፉ የሚችሉ ደም ወለድ ኢንፌክሽን ሊያጋልጥዎ የሚችሉ ባህሪያቶች ከነበርዎ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ በደምና በደም ዉጤቶች ሊተላለፉ የሚችሉ ኢንፌክሽኖች ስላሉ ሁሉም ሰዉ ደም መለገስ ላይችል ይችላል፡፡ ስለሆነም የሚከተሉት ሰዎች ደም ለመለገስ ብቁ አይደሉም:-
• ያለ ሀኪም ትዕዛዝ በመርፌ የሚወጉ እንደ ስቴሮይድና ህገወጥ መድሃኒቶችን የሚጠቀሙ/የተጠቀሙ ሰዎች
• ከዚህ በፊት ክሎቲይንግ ፋክተርስ መድሃኒቶችን የተጠቀሙ/ወስደዉ የሚዉቁ ሰዎች
• የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸዉ ያለባቸዉ ሰዎች
• የግብረስጋ ግንኙነትን ለገንዘብ ወይም ለህገወጥ መድሃኒቶች ማግኛ የሚጠቀሙ ግለሰቦች
• በደማቸዉ የሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ያለባቸዉ ሰዎች
የተወሰኑ አካለዊ ምርመራዎች( የደም ግፊትዎን መለካት፣ የሰዉነት ሙቀትዎንና የልብ ትርታዎ) ቼክ ሊደረግልዎ ይችላል፡፡ ትንሽ ደም ተወስዶ የቀይ የደም ሴልዎ መጠን ይታያል፡፡ ቀይ የደም ሴል መጠንዎ ችግር ከሌለበትና በሌሎች ምርመራዎችም ብቁ ከሆኑ ደም መለገስ ይችላሉ፡፡
ደም ከለገሱ በኃላ ለተወሰነ ጊዜ መቆያ ክፍል ዉስጥ እንዲያርፉ ተደርገዉ ቀለል ያሉ መክሰሶችንና የሚጠጡ ነገሮችን እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡ ከዚያን ከ 15 ደቂቃዎች በኃላ ወደ ጉዳዮ እንዲሄዱ ይደረጋሉ፡፡

ደም ከለገሱ በኃላ፡-
• ተጨማሪ ፈሳሽ ለቀጣይ አንድ ወይም ሁለት ቀናት መዉሰድ
• ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከባድ ስራ ያለመስራት/ከባድ ዕቃ ያለማንሳት
• የራስ ምታት/የማዞር ስሜት ከተሰማዎ ስሜቱ እስኪያልፍልዎ ለተወሰነ ጊዜ እግርዎን ወደላይ አድርገሁ ይንጋለሉ፡፡
• ደም ለመለገስ የተወጉበት ቦታ ላይ የታሰረልዎን ባንዴጅ/ፕላስተር ቢያንስ ከ4-5 ሰዓታት ያለመፍታት
• ባንዴጁን/ፕላስተሩን ከፈቱ በኃላ ቢደማብዎ ቦታዉ ላይ ጫን አድርገዉ በመያዝና እጅዎን ከፍ አድርገዉ በመያዝ ለአምስት ደቂቃዎች መቆየት
• መርፌ የተወጉበት ቦታ ላይ ባለዉ ቆዳዎ ስር ደም መፍሰስ ወይም መቅላት ካለዎ በረዶ አልፍ አለፍ እያሉ ለመጀመሪያ 24 ሰዓታት መያዝ
• እጅዎን ካመመዎ እንደ አሴታሚኖፌን/ፓራስታሞል ያሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን መዉሰድ፡፡ ነገር ግን እንደ አስፒሪን ወይም አይቡፕሮፌን(አድቪል) የመሳሰሉ መድሃኒቶችን ከመዉሰድ ይቆጠቡ፡፡

ደም ከለገሱ በኃላ የሚከተሉት ችግሮች ከቀጠሉ/ካሉ የህክምና ባለሙያ/ ያማክሩ/ለቀይ መስቀል ያሳዉቁ:-
• በቂ እረፍት፣ፈሳሽና ምግብ ከወሰዱ በኃላ ማዞር፣ ማቅለሽለሽና የራስ ምታቱ ከቀጠለ
• መጠዝጠዝ/ህመም በእጅ ጣትዎ ላይ ከተሰማዎ
• ደም ከለገሱ በአራት ቀናት ዉስጥ የጉንፋን ምልክቶች ከታየብዎ (ትኩሳት፣ የራስምታት፣ የጉሮሮ ህመም)፡፡ ይህ የሚያስፈልግበት ምክንያት ባክቴሪያ የእርስዎን ደም ወደሚወስደዉ ሰዉ እንዳይተላለፍ ነዉ፡፡

ዉጤቶች
እርስዎ የሰጡት ደም የተለያዩ ምርመራዎች ይደረጉበታል
• የደም አይነት፡- አራት አይነት የደም አይነቶች ያሉ ሲሆን እነርሱም ኤ፣ቢ፣ኤቢና ኦ ናቸዉ፡፡ በተጨማሪም የደምዎ አር ኤች አይነት ቼክ ይደረጋል (አር ኤች ኔጋቲቭ ወይም ፖዘቲቭ ለመሆኑ)
• በደም ምክንያት ሊተላለፉ የሚችሉ እንፌክሽኖች መኖር አለመኖራቸዉን ማረጋገጥ፡-ለሄፓታይትስ፣ ኤች ኤቪ፣ ሲፍሊስ(ቂጥኝ)ና ለመሳሰሉት ከተመረመረ በኃላ ደሙ ምንም ችግር ከሌለበት ለህሙማን እንዲሰጥ ለየሆስፒታሉ ይከፋፈላል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ አንዱ እንኳ ከተገኘ ደሙ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ይደረጋል፡፡

ለአፍንጫ መድማት/ ነስር ሊደረግ የሚችል የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናነስር በጣም የተለመደ የአፍንጫ መድማት ችግር ነዉ፡፡ ይህ ክስተት ብዙዉን ጊዜ የሚመጣዉ በመሰረታዊ የጤና ችግር ምክንያት ያል...
21/05/2021

ለአፍንጫ መድማት/ ነስር ሊደረግ የሚችል የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና

ነስር በጣም የተለመደ የአፍንጫ መድማት ችግር ነዉ፡፡ ይህ ክስተት ብዙዉን ጊዜ የሚመጣዉ በመሰረታዊ የጤና ችግር ምክንያት ያልሆነና ሊረብሽዎ/ሊያናድድዎ የሚችል ችግር ነዉ፡፡

ሊደረግ የሚችል እንክብካቤ
• ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ትንሽ ዘንበል ብሎ መቀመጥ፡- ቀጥ ብሎ መቀመጥ የአፍንጫዎን የደም ግፊት መጠን ለመቀነስ ያግዝዎታል፡፡ ወደፊት ማዘንበልዎ ደግሞ ደሙን እንዳይዉጡት ለመከላከል ይረዳዎታል፡፡
• አፍንጫዎን ጫን አድርገዉ/ቆንጥጠዉ መያዝ፡- አፍንጫዎን በአዉራ ጣትዎና በጠቋሚ ጣትዎ ከ5 እስከ 10 ደቂቃዎች በደንብ በመያዝ የአፍንጫ ቀዳዳዉን አፍኖ መቆየትና በአፍዎ መተንፈስ፡፡ አፍንጫዎን በደንብ አድርገዉ መያዝ በሚደማዉ የደም ቧንቧ ላይ ግፊት ስለሚፈጥር መድማቱን እንዲያቆም ያደርጋል፡፡
• በድጋሚ እንዳይደማ መከላከል፡- የአፍንጫዎ መድማት ካቆመ በኃላ ለተወሰኑ ሰዓታት አፍንጫዎን ያለመጎርጎር ፣ ያለመናፈጥና ወደታች ያለማጎንበስ፡፡ በዚህን ጊዜ በተቻለ መጠን የራስ ቅልዎን/አፍንጫዎን ከልብዎ በታች ያለማድረግ፡፡
• እንደገና መድማት ካጋጠመዎ፡- እንደገና መድማት ካጋጠመዎ የረጋዉን ደም ለማሶጣት መናፈጥ፤ ከዚያን ኦክሲሜታዞሊን ናዛል ዲኮንጀስታንት ስፕሬይ በአፍንጫዎ በሁለቱም በኩል መርጨት፡፡ አፍንጫዎን እንደገና ከላይ በተጠቀሰዉ መንገድ መያዝና የህክምና ባለሙያዎን ማማከር፡፡

ድንገተኛ ህክምና ማግኘት የሚገባዎ መቼ ነዉ?
• መድማቱ ከ20 ደቂቃዎች በኃላ ከቀጠለ
• የአፍንጫ መድማቱ አደጋን ተከትሎ የመጣ ከሆነ (የመዉደቅ፣መመታት)

የህክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
• በተደጋጋሚ መንሰር ካጋጠመዎ
• የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች እየወሰዱ ነስር ካጋጠመዎ፡- እንደ ዋርፋሪንና አስፒሪን የመሳሰሉ መድሃኒቶችን እየወሰዱ ከሆነና የአፍንጫ መድማት ካጋጠመዎ መድሃኒቱን ማስተካከል ሊያስፈልግ ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር፡፡

ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች  በሙሉ እንኳን ለስቅለት በዓል እንዲሁም  የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም እራሳችንንና አካባቢያችንን እን...
29/04/2021

ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለስቅለት በዓል እንዲሁም የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም እራሳችንንና አካባቢያችንን እንጠብቅ፡፡
በዓሉ የሰላምና የጤና እንዲሆንላችሁ 8896 ሃሎ ዶክተር ይመኛል፡፡

የቶንሲል ህመም/ ቶንሲላይቲስ/ Tonsillitisየቶንሲል ህመም/ቶንሲል በቶንሲል መቆጥቆጥ ምክንያት የሚከሰት ነዉ፡፡ ብዙዉን ጊዜ የቶንሲል ህመም የሚከሰተዉ በቫይረስ እንፌክሽን ሲሆን በባክ...
29/04/2021

የቶንሲል ህመም/ ቶንሲላይቲስ/ Tonsillitis
የቶንሲል ህመም/ቶንሲል በቶንሲል መቆጥቆጥ ምክንያት የሚከሰት ነዉ፡፡ ብዙዉን ጊዜ የቶንሲል ህመም የሚከሰተዉ በቫይረስ እንፌክሽን ሲሆን በባክቴሪያ ኢንፌክሽንም ሊመጣ ይችላል፡፡

የቶንሲል ህመም ምልክቶች
የቶንሲል ህመም በብዛት የሚያጠቃዉ ህፃናትን ሲሆን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፡፡
• የቶንሲል መቅላትና እብጠት
• የቶንሲል መከርከር
• ምግብ በሚዉጡበት ወቅት ህመም መኖር/ መዋጥ መቸገር
• ትኩሳት
• በአንገት ላይ ያበጡና ህመም ያላቸዉ ዕጢዎች መከሰት
• የድምፅ መቀየር
• መጥፎ የአፍ ሽታ
• የሆድ ህመም( በተለይ በእድሜያቸዉ ትናንሽ ህፃናት ላይ)
• የአንገት ህመም/መጠንከር
• የራስ ምታት ናቸዉ፡፡
በጣም ጨቅላ በሆኑ ህፃናትና የህመማቸዉን ሁኔታ መግለፅ በማይችሉ ህፃናት ላይ
• ሲዉጡ ህመም ስላላቸዉ የምራቅ/ለሃጭ መዝረከርክ
• ምግብ መመገብ እምቢ ማለትና
• ያልተለመደ ድካም የህመሙ ምልክቶች ናቸዉ፡፡
የህክምና ባለሙያ ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
• በ24 ሰዓታት ዉስጥ ለዉጥ የሌለዉ የቶንሲል ህመም ካጋጠመዎ
• ምግብ ሲዉጡ ህመም ካለዎና
• የድካም/የመዝለፍልፍ ስሜቶች ከፍ ያለ ከሆኑ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
ለቶንሲል ህመም የሚያጋልጡ ነገሮች
• ለጋ እድሜ፡- የቶንሲል ህመም ትናንሽ ህፃናትንና ለጋ እድሜ ላይ ያሉ ልጆችን በብዛት ያጠቃል፡፡
• በተደጋጋሚ ኢንፌክሽኑን ለሚያመጡ ጀርሞች መጋለጥ፡- በትምህርት ቤት የሚዉሉ ህፃናት ከአቻዎቻቸዉ ጋር ያላቸዉ የቀረበ ግንኙነት/ንክኪ ለቫይረሶችና ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡

የቶንሲል ህክምና
1. የቤት ዉስጥ ህክምና
የቶንሲል ህመሙ በቫይረስም ይሁን በባክቴሪያ ምክንያት ቢከሰትም የቤት ዉስጥ ህክምናዎችን መከወን ምቾት እንዲሰማዎና ቶንሲሉ ቶሎ እንዲድን ያደርገዋል፡፡ የቶንሲል ህመሙ የተከሰተዉ በቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ የህክምና ባለሙያዎ ምንም ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት ስለማያዝልዎ ህመሙ እንዲድን የቤት ዉስጥ ህክምና ማከናወን የህክምናዉ ዋናዉ አካል ነዉ፡፡ የቶንሲል ህመም በ10 ቀናት ዉስጥ ሊሻሻል ይችላል፡፡

ሊደረጉ የሚችሉ የቤት ዉስጥ ህክምናዎች
• በቂ እረፍት ማግኘት፡- ብዙ ያለማዉራትና በቂ እንቅልፍ ማግኘት
• ፈሳሽ በበቂ መጠን መዉሰድ
• ምቾትን ሊሰጡ የሚችሉ ምግቦችን መመገብ፡- ትኩስ ፈሳሾች እንደ ሾርባ፣ካፊን የሌለዉ ሻይ፣ የሞቀ ዉሃ በማር እንዲሁም ቀዝቃዛ የሆኑ እንደ በረዶ ያሉ ነገሮች የጉሮሮ መከርከርን ሊያክሙ ይችላሉ፡፡
• ጨዉ ባለዉ ዉሃ አፍን መጉመጥመጥ
• ወደ ዉስጥ የሚገባዉን አየር እርጥበታማ/ሂሙድፋይ እንዲሆን ማድረግ፡- ወይ የቀዝቃዛ አየር ሂሙድፋየር መጠቀም አለዚያ ደግሞ እንፋሎት መታጠን ደረቅ አየር ጉሮሮ ላይ የሚያመጣዉን መከንከን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
• ሊቆጠቁጡ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ፡- ጉሮሮን ሊከረክሩ ከሚችሉ እንደ የሲጋራ ጭስና የቤት ማጽጃ ኬሚካሎች እራስን መጠበቅ
• ህመምና ትኩሳት ካለ ማስታገሻ መዉሰድ፡- እንደ ፓራሲታሞላና አይቡ ፕሮፌን ያሉ መድሃኒቶችን መጠቀም፡፡
2. መድሃኒቶች
የቶንሲል ህመም የተከሰተዉ በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከሆነ የግድ ፀረ-ባክቴሪያ መድሃኒቶችን (አንቲባዮቲክሶችን) መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡ በህክምና ባለሙያዎ የታዘዘልዎትን መድሃኒት በአግባቡ ወስዶ መጨረስ የሚያስፈልግ ሲሆን በአግባቡ ካልተወሰደ ግን ባክቴሪያዉ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰራጭ፤ህፃናት ላይ ደግሞ የልብ ህመም እንዲከሰት መንስኤ መሆንና ቀጣይነት ያለዉ የቶንሲል ህመም (ክሮኒክ ቶንሲላይትስ) እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
የቶንሲል ህመምን መከላከል
ቶንሲልን ሊያመጡ የሚችሉ ጀርሞች (ባክቴሪያና ቫይረስ) ከሰዉ ወደ ሰዉ ተላላፊ ናቸዉ፡፡ ስለሆነም የቶንሲል ህመምን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች ዉስጥ ዋነኛዉ የግል ንፅህናን መጠበቅ ነዉ፡፡ እራስዎም ሆኑ ልጆችዎ
• ምግብ ከመመገባችሁ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት መልስ እጃችሁን በደንብ መታጠብ
• የመጠጫና መመገቢያ እቃዎችን በጋራ ያለመጠቀም ይመከራል፡፡
ልጆች የቶንሲል ህመም ካላቸዉ ኢንፌክሽኑን ወደሌሎች እንዳያዛምቱ
• ልጅዎ ታሞ ከሆነ ለተወሰነ ቀናት እቤት እንዲቆይ ማድረግ
• ልጅዎ መቼ ት/ት ቤት መሄድ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር
• ልጅዎ በሚስልበትና በሚያስነጥስበት ወቅት አፍና አፍንጫዉን በሶፍት ወይም በክርኑ የዉስጠኛዉ ክፍል እንዲሸፍን ማስተማርና
• ልጅዎ ካሳለዉ ወይም ካስነጠሰዉ በኃላ እጁን/እጇን እንዲታጠቡ ማስተማር ናቸዉ፡፡

ህፃን ልጅዎ የዘጠኝ ወር እድሜ ሳለከዚህ በፊት የህፃን ልጅዎን የአጨዋወት፣ አነጋገር/ ቋንቋ፣ እንዴት እንደሚማር እና እንቅስቃሴዎችን እንዴት እንደሚተገብር በመከታተል ስለልጅዎ የእድገት ሁኔ...
20/04/2021

ህፃን ልጅዎ የዘጠኝ ወር እድሜ ሳለ

ከዚህ በፊት የህፃን ልጅዎን የአጨዋወት፣ አነጋገር/ ቋንቋ፣ እንዴት እንደሚማር እና እንቅስቃሴዎችን እንዴት እንደሚተገብር በመከታተል ስለልጅዎ የእድገት ሁኔታ ፍንጭ ማግኘት እንደሚቻልና የ 6 ወር ህፃን ሊያሳይ የሚችላዉን ነገሮች መነጋገራችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከዚያ የቀጠለ የዘጠኝ ወር ልጅን የእድገት ክትትል እናያለን፡፡

ሕፃናት በዚህ እድሜ ምን ነገሮችን ሊተገብሩ ይችላሉ?

ማህበራዊና ስሜታዊ ነገሮች / Social and Emotional
• እንግዳ የሆኑ ሰዎችን መፍራት
• የሚመርጧቸዉ/የሚወዷቸዉ መጫወቻ/አሻንጉሊቶች ይኖራቸዋል
• የሚያዉቋቸዉን ሰዎች በጣም ይቀርባሉ

ቋንቋ/ መግባባት/ Language/Communication
• አይሆንም ሲባሉ መረዳት መቻል
• እንደ ማማማማ ና ባባባ የሚሉ የተለያዩ ድምፆችን ማዉጣትመቻል
• የሌሎችን ድምፅና የሰዉነት እንቅስቃሴ ማስመሰል መቻል
• ጣትን በመጠቀም ነገሮችን ለመጦቆም መቻል

ስነአዕምሮያዊ( የመማር፣የማሰብና ችግሮችን የመፍታት)/ Cognitive (learning, thinking, problem-solving)

• የሚወድቅ ነገር ካለ እቃዉ የሚሄድበትን መንገድ/አቅጣጫ መከተል
• ህፃኑ እያየ እየደበቁት ያለ እቃ ካለ መፈለግ መቻል
• አየሁሽ/ድብብቆሽ መጫወት መቻል
• ነገሮችን ወደ አፍ መክተት/መዉሰድ መቻል
• ያለምንም ችግር ነገሮችን/መጫወቻዎችን ከአንዱ እጅ ወደ ሌለኛዉ ማዘዋወር መቻል
• ትናንሽ ነገሮችን/ጥራጥሬ/ በአዉራ ጣትና በጠቋሚ ጣት ለመያዝ መቻል

እንቅስቃሴ/አካላዊ እድገት/ Movement/Physical Development

• ያለድጋፍ መቀመጥ መቻል
• ዕቃ ተደግፎ/ ይዞ ለመነሳት መሞከር/መቻል
• ከተኛበት ተነስቶ መቀመጥ መቻል
• ሲያዝ ለመነሳት መቻል
• መዳህ መቻል

በዚህ እድሜ ህፃን ልጅዎ የሚከተሉትን ነገሮች ማሟላት ካልቻለ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
• ያለ ድጋፍ ክብደቱን በእግሮቹ መደገፍ/መሸከም የማይችል/የሚሳነዉ ከሆነ
• ያለድጋፍ መቀመጥ ካልቻለ
• የተለያዩ ድምፆችን( ማማ፣ባባ፣ዳዳ) ማለት ካልቻለ
• ማንኛዉንም አይነት ጨዋታ መጫወት ካልቻለ
• በራሱ ስም ሲጠራ ምንም አይነት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ
• የሚታወቁ/የቅርብ ሰዎችን መለየት የማይችል ከሆነ
• ወደሚያመለክቱበት አቅጣጫ የማይመለከት ከሆነ
• መጫወቻዎችን ከአንዱ እጅ ወደ ሌለኛዉ ማዘዋወር የማይችል ከሆነ የህክምና ባለሙያን ለማነጋገር ይሞክሩ፡፡

የእትብት እንክብካቤ፡-መደረግና መደረግ የሌለበት ነገሮችአዲስ ለተወለደ ልጅዎ ለእትብቱ ማድረግ ስለሚገባዉ እንክብካቤ ግራ ተጋብተዋል? የእትብቱ የመዳን እንዲፋጠን የሚከተሉትን ምክሮች መተግበ...
02/04/2021

የእትብት እንክብካቤ፡-
መደረግና መደረግ የሌለበት ነገሮች

አዲስ ለተወለደ ልጅዎ ለእትብቱ ማድረግ ስለሚገባዉ እንክብካቤ ግራ ተጋብተዋል? የእትብቱ የመዳን እንዲፋጠን የሚከተሉትን ምክሮች መተግበር ይችላሉ

የልጅዎ እትብቱ የጠቋጠረበት ቦታ እየደረቀ ሲመጣ ከነጭ ሰማያዊ መልክ ወደ ጥቁርነት እየተቀየረ መጥቶ በስተመጨረሻ ከእንብርቱ ላይ ተገንጥሎ ይወድቃል፡፡ ይህ ሂደት እስከ ሶስት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ እስከዚየዉ ግን ቦታዉን በደንብ/በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

·የተቋጠረበትን ቦታ በንፅኅና መያዝ፡- እትብቱ የተቋጠረበት ቦታ ንፅህና ከሌለዉ ወይም የሚያጣብቅ ከሆነ በዉሃ በደንብ ካፀዱ በኃላ ንፁህ ጨርቅ በቦታዉ ላይ በመያዝ ማደራረቅ

·እትብቱ የተቋጠረበትን ቦታ ደረቅ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ፡- እትብቱ የተቋጠረበት ቦታ አየር እንዲያገኝ በማድረግና እንዲደርቅ ማድረግ፡፡ ከፊት ለፊት(ሆዱ ላይ) ያለዉን የህፃኑን ዳይፐር/የሽንት ጨርቅ እትብቱን እንዳይሸፍነዉ ወደታች ማጠፍ፡፡ ሙቀት በሚሆንበት ወቅት ልጁን በዳይፐርና በቲሸርት ብቻ እንዲሆን በማድረግ አየር በደንብ እንዲዘዋወርበት ማድረግ

·የእትብቱን ቦታ በንፁህ ጥጥ ማፅዳት፡- እትብቱ እየዳነ ባለበት ወቅት በጥጥ ቦታን ማፅዳት፤እትብቱ ከወደቀ በኃላ ግን ቦታዉን ገላዉን ሲታጠብ አብሮ ማጠብ

እትብቱ እንፌክሽን በሚፈጥርበት ወቅት የሚኖረዉ ምልክት

አትብቱ እየዳነ ባለበት ወቅት እትብቱ ከተsጠረበት አካባቢ ትንሽየ መድማት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ሂደት ችግር የለዉም፡፡እትብቱ ተቆርጦ በሚወጣበት ወቅትም ትንሽየ ደም መታየቱ የተለመደ ነዉ፡፡ ነገር ግን እትብቱ ከተቋጠረበት አካባቢ መግል ካለ ወይም በእትብቱ ዙሪያ ያለዉ ቆዳ ካበጠ ወይም ከቀላ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ልጅዎ የእተትብት እንፌክሽን ካለዉ እንፎክሽኑ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዛመት የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡

እስከ ዛሬ ድረስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ 2,510 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።
12/03/2021

እስከ ዛሬ ድረስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ 2,510 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ ከፍተኛውን የሞት ቁጥር አስመዘገበች።
***************************
የመጀመሪያውን በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ሪፖርት ካደረግን አንድ አመት ሊሞላው አንድ ቀን ሲቀረው እንዲሁም የኮቪድ-19 ቫይረስ ክትባት ልንሰጥ አንድ ቀን ብቻ ሲቀረን ከፍተኛውን የሞት ቁጥር አስመዘገብን።
በዛሬው እለት 27 ግለሰቦች በአንድ ቀን በኮቪድ-19 ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን እንደዚህ አይነት ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበው ከአስከሬን ላይ ናሙና ወስደን በምንመረምርበት ወቅት ነበር።
እስከ ዛሬ ድረስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ 2,510 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል። እስከ ዛሬው እለት 454 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ ይህም ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
መዘናጋቱ በዚሁ ከቀጠለ ነገ የእያንዳንዱን ቤት ማንኳኳቱን ሰለማይቀር አሁንም የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ሕብረተሰቡ እንዲተገብር የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሳስባል።
#ይብቃ
#እንድናገለግልዎማስክዎንያድርጉ


https://t.me/EthPHI
https://www.facebook.com/EPHIEthiopia

Address

Addis Ababa
00000

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when 8896 Hello Doctor Ethiopia posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share

Share on Facebook Share on Twitter Share on LinkedIn
Share on Pinterest Share on Reddit Share via Email
Share on WhatsApp Share on Instagram Share on Telegram

Category