26/11/2022
እውን ምሁር አለን?
(በይሁኔ አየለ)
(ማስታወሻ፡- ይህን ጽሁፍ የፃፍሁት ዲላ ዩኒቨርሲቲ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር በሚያውጣው “የዲላ ዩኒቨርሲቲ የ25 ዓመታት ጉዞ ልዩ መጽሔት” እንዲወጣ ነበር፡፡ በዓሉ ይከበራል ተብሎ የተቆረጠው ቀን ብዙ ወራት አለፉት፡፡ አሁንም፣ አከባበሩ ላተወሰነ ጊዜ ተላልፏል የሚል መረጃ ሰማሁ፡፡ የጽሁፌ ዓላማ አጅንዳው በወያያ እንዲሆን ነው፡፡ ስለሆነም ፌስቡክን ተጠቅሜ ለአንባቢዎች አቅርቤዋለሁ፡፡ እንወያይበት፡፡)
……………….
ለከት ባጣ መልኩ ጥቅም ላይ እያዋልናቸው ካሉ ቃላትና ጽንሰ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ ‘ምሁር’ የሚለው ይገኝበታል፡፡ አገራችን በ‘ምሁር’ ስም ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ ‘የተማረ ይግደለኝ’ በሚል ማኅበረሰብ ዘንድ በምሁር ካባ ተጀቡነው መንጋውን የሚነዱ፣ መሪዎችንና ህዝቡን የሚያደናግሩና ‘ምሁርነቱ’ በፈጠረላቸው መብት ከአቅማቸው በላይ የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ በቃሉ አጠቃቀም ዙርያ ግልጽና ትክክለኛ አረዳድ ይኖር ዘንድ አጀንዳ አድርጎ ለውይይትና ክርክር በር መክፈት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
'ምሁር ማነው?' ወደሚለው ጥያቄ ለማምራት የሚያግዘኝ አንድ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ላንሳ፡- ሸክላ ሥራን፡፡ ዛሬ በየቤታችን ያሉት በርካታ ከሸክላ የተሠሩ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ ቁሳቁሶች አጀማመርና እድገት ስናስብ:- (1) ከማንም በፊት የአፈሩ ዓይነት ተለይቶ፣ ተፈጭቶ፣ ተቦክቶ፣ ሸክላው ተሠርቶ፣ ደርቆና ተተኩሶ ሸክላ ሊፈጠር እንደሚችል የፈለሰፈውን ሰው ወደ እሳቤያችን ይመጣል፡፡ (2) የፈልሳፊውን ሀሳብ ተከትለው ሸክላ በተለያዩ ቅርጾችና መጠኖች (ፕሮቶታይፖች) ሊሠራና ለተለያዩ የቤት ቁሳቁሶች (እንስራ፣ ድስት፣ ምጣድ፣ ጀበና፣ ሳህን ወዘተ.) ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ቁሳቁሶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ቅርጽ አስይዘው የሠሩትን ሰዎች እናስባለን፡፡(3) የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ቁሳቁሶችን ከሠሩ በኋላ እነሱን እየተከተሉና ከእነሱ እየተማሩ በየዘመናቱ ሸከላ በመሥራትና በማምረት እየተዳደሩ የሸክላ ውጤቶችን እያመረቱ የሚያቀርቡልንን ባለሙያዎች እናስባለን፡፡ በአጠቃላይ በሸክላ ሥራ ሦስት ዐይነት ባለሙያዎችን እናገኛለን፡፡ (1) የሸክላ ሥራ ሐሳብ አፍላቂ (ምናልባትም አንድ ብቸኛ ሰው ልትሆን ትችላለች)፣ (2) ከሸክላ በተለያዩ ቅርጽና መጠን (ፕሮቶታይፕ) ቁሳቁሶችን የሚፈጥሩ ጠቢባን፣ (3) ጠቢባን የፈጠሯቸውን ፕሮቶታይፖች ኮርጀው ሸክላ የሚያመርቱ ሠሪዎች፡፡ በአጭሩ ፈልሳፊ፤ ጠቢብና ሠራተኛ እንበላቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ሚናዎች በማንኛውም ሙያና ዲሲፕሊን ውስጥ አሉ፡፡ በማኅበራዊ ሳንይንሱ፣ በተፈጥሮ በሳይንሱና ቴክኖሎጂው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሀሳብ እንያዝና “ምሁር ማን ነው?” ወደሚለው ጥያቄ እንመለስ፡፡
ምሁር የሚለው ቃል በእንግሊዝኛው ‘ኢንቴሌክቹዋል’ (intellectual) የሚለውን ቃል ይተካል፡፡ ኢንቴሌክቹዋል የሚለው ቃል ኢንተሌክት (Intellect) ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን ኢንተሌክትን የኦክስፎርድ ላንጉዌጅስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይፈታዋል፡- ‹‹ርቱእ በሆነ መንገድ ምጡቅ ጉዳዮችን የማሰብ (የማጠየቅ) እና የመገንዘብ ችሎታ (the faculty of reasoning and understanding objectively, especially with regard to abstract matters.)፡፡ ምሁር የሚለውን ቃለ ደግሞ የላቀ የምክነያ (reasoning) ባለቤት የሆነ ሰው (a person possessing a highly developed intellect.) በማለት ይፈታዋል፡፡
ይህን ብያኔ ተከትለን ስሄድ ምሁርነት በዋናነት ሁለት መገለጫዎች እዳሉት እንረዳለን፡፡ አንደኛው አስተሳሰቡ ርቱእ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ርቱእ ነው›› ማለት ሐሳቡ ከግላዊ ስሜቱና ልምዱ የተቀዳ ሳይሆን ከተጠየቃዊ አመክንዮ የሚመነጭ ማለት ነው፡፡ ሰለዚህም ሃሳቡ ቅቡል የመሆኑ ዕድል የሰፋ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አስተሳሰቡ የላቀ፣ ምጡቅ መሆኑ ነው፡፡ ምሁር አብዛኛው ህብረተሰብ ይሁነኝ ብሎ የሚቀበላቸውን ነገሮች በዘልማድ አይቀበልም፡፡ ለምን፣ እንዴት፣ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ተጠየቃዊ በሆነ ምክነያም መልስ ይፈልጋል፡፡ በመጨረሻም ያገኘውን መልስ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ያካፍላል፡፡
የምሁራንን ቅቡል አስተሳሰቦች ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ያሰራጩላቸዋል፡፡ የምሁራንን አስተሳሰብ በማባዛት፣ በማሰራጨት፣ በመተግበር የተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ኢንተልጀንሺያ (Intelligensia) ተብሎ ይጠራል፡፡
ይህን ግንዛቤ ይዘን ከመነሻችን ላይ ካነሳነው የሸክላ ሥራ ጋር የተያያዙ ሦስት አካላትን እንመርምር፡፡ በምሳሌው መሠረት በሸክላ ሥራ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት ሦስት አካላት በምሁርነት ሊፈረጅ የሚችለው የትኛው ነው ብለን እንጠይቅ፡፡ በሌላ አነጋገር የሸክላ ሥራን በሚመለከት ነባራዊና ምጡቅ አስተሳሰብ ያበረከቱት አካላት የትኞቹ ናቸው ብለን ደግመን እንጠይቅ፡፡ ፈልሳፊው? ተጠባቢው? ወይስ ሸክላ ሠሪው?
እንደሚመስለኝ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ብቻ በምሁርነት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ማንም የማያስበውን ነገር አስቦ ከአፈርና ውሃ ሸክላ ሊፈጠር እንደሚችል በምክንያ አስቦ ችግር ፈቺ ሸክላን ፈጠር፤ ጠቢባኑ ደግሞ በፈልሳፊው ሀሳብ ላይ ተመሥርተው እንደየባህላቸውና እንደየህብረተሰባቸው ፍላጎት የተለያዩ ፕሮቶታይፖችን እየፈጠሩ ለሸክላ ሠሪዎቸ አስተማሩ፡፡ ከዘያ በኋላ የነዚህ የሁለቱ ምሁራን አስተሳሰብ በግለሰቦችና በማህበራዊ ተቋማት በትምህርትነት እየተሰጠና እየተስፋፋ በኢንተልጀንሺያ (ሸክላ ሠሪና አስተማሪ) አማካኝነት ለህበረተሰብ ሲጠቅምና ባህል ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ይኖራል፡፡
ይህን ቀላል ግንዛቤ ይዘን ወደአገራዊ ነባራዊ ሁነታችን እንመለስ፡፡ ለመሆኑ ምሁር አለን? ምሁራን ካሉን አነማን ናቸው? ከሌሉንስ ደግሞ ለምን የሉንም ወደሚለው ሀሳብ እንሸጋገር፡፡
ኢትዮጵያ ምሁራን አሏትን?
ከላይ የተሰጠውን የምሁራን ብያኔ ተንተርሰን ኢትዮጵውያን ምሁራንን ፈለጋ ብንሰማራ ማን ማንን እናገኛለን? መጀመሪያ ልክ እንደሸክላ ሥራ ፈልሳፊዎች ያሉ አዲስ ነገርን ተጠየቃዊ በሆነ አመክንዮ አማካኝነት ፈጥረው ለአገራችን ወይም ለዓለም ያበረከቱ ኢትዮጵያውያን እነማን ናቸው ብለን ስንፈልግ ገጥጦ የሚታየን ምሀር አልባነታችን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምናልባት ፈላስፋው ዘረአ ያዕቆብንና ተማሪውን ወልደ ህይወትን እንዲሁም የዜማ ፈጣሪውን ቅዱስ ያሬድን ልንጠቅስ ከመቻላችነ ውጭ ሌላ አፋችንን ሞልተን አገሌ ልንለው የምንችለው አንድም ሰው ያለን አይመስለኝም፡፡ የእንዲህ አይነት ምሁራን መድረ በዳ ነን፡፡
ይህን ስንል ግን ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ምንም ነገር የለም ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የነአክሱም፣ ሀረር፣ ላሊበላና ጎንደር ኪነ ህንጻዎች፣ ለምዕራባውያን ዘመናዊ የመድኃኒት ቅመማ መሠረት የሆኑ ባህላዊ መድኃኒቶቻችን፣ እደ ገዳ ሥርዓት (ዘመን ተሻግረው እኛ ዘመን የደረሰውን እንጂ በአላዋቂ ፖለቲካችን ያበሻቀጥነውን እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ) የመሠሉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን አበርክተናል፡፡ ሆኖም እነዚህን ትሩፋቶች ያበረከቱልን ምሁራን ቅድመ ታሪክ ያለፉ በመሆናቸው ስም ልንጠቅስ አንችልም፡፡ ያም ሆነ ይህ በፈልሳፊ ምሁራን እይታ ምሁር አልባ ነን፡፡ አለቀ!
በሁለተኛ ምድብ ማለትም ፈላስፎች የፈለሰፏቸውን ሀሳቦች ለራሳችን ማህበረሰብ እንዲስማማ አድርጎ መልሶ በመቀመር ረገድ ያሉንን ምሁራን እንፈልግ፡፡ በዚህ ረገድ ምናልባት የተወሰኑ በጣት የሚቆጠሩ ምሁራንን ልንጠቅስ እንችላል፡፡ ለአብነትም ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን፣ እጓለ ገብረ ዮሐንስን፣ ሀዲስ አለማየሁና መስፍን ወልደማርያምን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ምሁራን ስለኢኮኖሚክስ፣ ስለትምህርት፣ ስለሀገርና መንግሥት አስተዳደር፣ ወዘተ. ያወቁትንና የተረዱትን ነገር ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስማማት እንዴት መሆን እንዳለበት ምክረ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፤ ምክረ ሀሳቦቻቸውን ምን ያህል ተጠቅመንባቸዋል የሚለው ጥያቄ እንተጠበቀ ሆኖ፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን በየሙያ መስኩ ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ተምረው በየትምህርት ተቋማቱና በየመሥሪያ ቤቱ/ በየድርጅቱ የተማረው የማኅበረሰብ ክፍል ምሁር ተብሎ ለመጠቀስ የሚያበቃው ምንም ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ያለው ኢትዮጳያዊ ሁሉ ኢንተልጀንሺያ ነው አልያም ደግሞ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያ (Pseudo intelligensia)፡፡
ኢንተለጀንሺያ ከላይ እንደገለጽነው የምሁራንን ሀሳብ በማስተማር፣ በማሰራጨትና በመተግባር ላይ የተሰማራ ነው፡፡ መምህሩ፣ ሀኪሙ፣ ጋዜጠኛው፣ ባለሙያው/ኤክስፐርቱ፣ ቴክኒሺያኑ፣ መሀንዲሱ ወዘተ. ሁሉ በዚህ ምድብ የሚካተት ነው፡፡ የኢንተለጀንሺያ የህይወት ጥሪውም ሆነ ተልእኮው የምሁራንን የአእምሮ ውጤት በሚገባ ተረድቶ ማስተማርና መተግበር ብቻ ነው፡፡ ይህን ካደረገ በቂው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ለምሁርነት አያበቃውም፡፡ ምሁር ለመሆን በተማረውና በሚተገብረው ነገር ላይ ተመራምሮና ተፈላስፎ አዲስ ነገር መጨመር አለበት፡፡ ይህን የሚያደርግ ኢንተሊጀንሺያ ምናልባትም ከብዙ ሺህ አንድ ቢገኝ ነው፡፡ ለዚህ የበቃ ኢንተለጀንሺያ ወደ ምሁርነት ከፍ አለ ይባል፡፡ ስለዚህም ኢንተለጀንሺያ የምሁራን መፍለቂያ ባህር ነው፡፡
በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ትልቁ የዱክትርና ዲግሪ ድረስ ባለው የ‹‹ተማረ›› ስብስብ ውስጥ ለኢንተልጀንሺያነትም ብቁ ያልሆነ ብዙ ሃሳዊ እንተለጀንሺያ (Pseudointelligensia) አለ፡፡ ሃሳዊ ኢንተለጀንሺያ ማለት ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› የምትለውን አገራዊ ብሂል ያፈረሰና ሳይማር ቆብ የጫነ ማለት ነው፡፡ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያ ስም እንጂ ዕውቀትና ግበር የለውም፡፡ የሚጠቀመውም በስሙ እንጂ በዕውቀቱና በግብሩ አይደለም፡፡ ሃሳዊ ኢንተለጀንሺያ ለተሰማራበት ሙያ ምንም አለማበርከቱ ሳያንስ ስሙን ብቻ ይዞ ሙያውን የሚያራክስ ነውረኛ ነው፤ ተላለኪ ነው፡፡ የተሰማራበትን ሙያ ዕውቀትና ምግባር ስለማያውቅ ሆዱን ለሞላለት ሁሉ ‹‹ ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት›› በማለት ራሱንም፣ ሙያውንም አዋርዶ አገርና ህብረተሰብን ወደ ኋላ ቀርነትና ቀውስ ይዞ ይጓዛል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን በእንዲህ አይነቱ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያ ተጥለቅልቃለች፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም በእንደዚህ ዓይነት ባለሙያዎች ነፃ አይደሉም፡፡ የመንግሥት ተቋማት ለተሰማሩበት ሙያ ብቁ ዕውቀት ሳይኖራቸው በተገዛ ዲግሪ አገርን ወደጥልቁ በሚጎትቱ ባለሙያዎች ተሞልተዋል፡፡ መሀንዲሶቻችን ለሃገራቸው የሚሆን መንገድ፣ ህንጻና ድልድይ መሥራት ተስኗቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎቻችን መውጪ አገር ኢንተልጀንሺያ እየተወረሩ ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶቻችን የተማሩትን የኢኮኖሚ ሳይንስ ከአገራችን ነባራዊ ሀኔታ ጋር አዋህደው እድገታችንን የሚተልም ሞዴል ማፍለቅ አቅቷቸው እስካሁን ለመተንበይም፣ ለማወቅም ያዳገተ ተአምራዊ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደሆንን አለን፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው መንግስታዊ መዋቅሮቻችን በሃሳዊ ኢንተለጀንሺያ ስለተሞሉ ይመስለኛል፡፡ ሃሳዊ እኒተለጀነንሺያ የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን እንጂ ዘመን ተሻግሮ በልጆቹና ወገኖቹ ላይ የሚደርሰው አደጋ አይታየውም፡፡ ይህን የማየት ዕውቀቱም ፍላጎቱም የለውም፡፡ ስለዚህም ስሙን ይዞ ይጓዛል፡፡
ወደተነሳሁበት ጥያቄ ተመልሼ፣ “ኢትዮጵያ ምሁር አላትን?” በዬ እንደገና ብጠይቅ፤ አንባቢያን ሁሉ መልሱን የሚነግሩኝ ይመስለኛል፡፡ በጭራሽ! ምሁራን የሉንም፡፡ የምሁራን ድርቀት ውስጥ ነን፡፡ ያለን የተወሰነ ኢንተልጀንሺያ እና ብዙ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያ ብቻ ነው፡፡ ስለዚሀም ምሁራን ከማለት እንታቀብ! ለመሆኑ የምሁራን ድርቀት ለምን መታን? ኢትዮጵያስ የምሁራን መካን ለምን ሆነች?
ኢትዮጵያን ለምን የምሁራን ድርቅ መታት?
አገራችን ለምን በቂ ምሁራንን ማፍራት አልቻለችም? ምሁራኑ የት ሄዱ? የተረጋገጡ የችግሩ መንስኤዎችን ማቅረብ ባይቻልም ብዙ ተገማች መንስኤዎችን ማቅረብ ግን አያዳግትም፡፡ በዋናነት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
1. የተንሸዋረረ ዘመናዊ ትምህርት፡- ዘመናዊ ትምህርትን የተቀበልንበትና የተቀረጽንበት ሥርዓተ ትምህርት (ይዘቱም፣ በዘዴውም፣ ቋንቋውም) ከአገራዊ ብሂሉ የተፋታ ነው፡፡ የዘመናዊ ትምህርታችን ይዘት ከነባራዊ ችግሮቻችንና ማንነታችን የተጨለፈ ሳይሆን ከባዕድ አስተሳሰብና ባህል የተወሰ ነው፡፡ የማስተማሪያ ዘዴያችንም አገር በቀል ከሆኑ ዘዴዎች ይልቅ የባዕድ ማስተማሪያ መንገድን እንዳለ የወረሰ ነው፡፡ የምንማርበት ቋንቋም ቢሆን እንዲሁ ባዕድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ታሪካችንን ሳይቀር በባዕድ ቋንቋ ነው የምናስተምረው፡፡ በመሆኑም የትምህርት ሥርዓታችን ማሰብንና ፈጠራን የሚያበረታታ ሳይሆን ተዘክሮን (መሸምደድና ማስታወስን) የብቃት መለኪያ አድርጎ የሚቀርጽ በመሆኑ ለችግሩ አንድ መንሥኤ መሆኑ አይካድም፡፡ የኛ ዘመናዊ ትምህርት ያቆጠቆጠው በራሳችን የትምህርት ጉቶ ላይ ይደለም፡፡ የኛ ትምህርትና ማሰብ ጨዋታ በሌሎች መጫወቻ ሜዳ ገብተን የምንጫወተው ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ አብነትን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ቅኔን የዓለም የፈጠራና የሐሳብ ማፍለቂያ የመጫዋቻ ሜዳ አድርገን ብናመጣው ከእኛ የበለጠ ማንም ሊራቀቅበት ባልቻለ ነበር፡፡
2. ስንዴና እንክርዳድን የማይለይ ማኅበረሰባዊ እሳቤ፡- ማኅበረሰቡ “የተማረ ይግደለኝ” በሚለው ውጉ ተደናግሮ ምሁራንን፣ ኢንተልጀንሺያንና ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያን የሚለይበትና የሚያነጥርበት (ብቁ የሆኑት አስመስክረው የሚወጡበት) ሥርዓታዊ አካሄድ የለውም፡፡ ህብረተሰባችን ሀሳዊ መሲህን እንጂ ሃሳዊ ምሁር ስለመኖሩ አይጠረጥርም፡፡ የተሻሉ ኢንተልጀንሺያ የሚባሉትም የራሳቸውን ዋጋ ከፍ ለማድረግና ገበያ ለመሳብ ባቆበቆቡ ሃሳዊ አንተልጀንሺያዎች (pseudo intelligentia) ተውጠዋል፡፡ ኢንተለጀንሺዎችም “ጊዜዬ አይደለም” በሚል የፍርሀት ይሁን የመሽኮርመም ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ በእርግጥ፣ ክስተቱ የዓለም አንድ ገጽታ ነው፡፡ የትኛውም አገር አውዳሚ መንግስት በጎኑ ሀሳዊ ኢንተልጀንሺያና ሃሳዊ ምሁራንን ማሰለፉ አይቀርም፡፡ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ማኦና ሂትለር የራሳቸው ደጋፊ፣ አጨብጫቢ፣ አድናቂና አስመሳዮች ነበሯቸው፡፡
3. ደህነት፡- በተለያዩ የእውቀት መስክ የሰለጠኑ ሰዎች ቢኖሩም በኢንተለጀንሺያነት ከመሥራት በዘለለ ወደ ምሁርነት ለማደግ ያለው ድህነት ከባድ ነው፡፡ የተማሩት ሰዎች ትኩረታቸው ኑሮን ለማሸነፍ ሲባል በሚችሉበት አግባብ (የባለሙያነት፣ የአድቮኬሲና አስፈፃሚነት ሙያ) ስለተጠመዱ፤ አዲስ ሐሳብ በማፍለቅ በደባባይም ሆነ መጽሐፍትን በመፃፍ አቅጣጫ ሲያመላክቱ አይታዩም፡፡ ብዙዎች ተቀጣሪ በመሆን በዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ውስጥ በመመርያ በታጠረ አሰራር ከሳጥኑ ውጭ እንዳያስቡ ሆነው የአካዳሚውን መሰላል ወደ ላይ ለመውጣት ብቻ በሰለጠኑባት መስክ ተቀርቅረው ጊዜያቸውን በመግደል ላይ ናቸው፡፡ ተቋማቱም በውስጣቸው የሚገቡ ሰዎች ሃሳዊ እንተልጀንሺያ እንዳይሆኑ ለመከላከል ብለሃት አልቀየሱም፡፡ ኢንተለጀንሺያ ከሆኑት መካከል ደግሞ ወደ ምሁርነት ሊያድጉ የሚችሉት የሚያድጉበትና ሥርዓትና ዕድል አልፈጠሩም፡፡ ይህን መፍጠር የቁሳቁስም ሆነ ነጻነትን የመፍቀድ ጥያቄ ስለሚኖረው ለመፈጸም አቅሙም ፍላጎቱም ያንሳቸዋል፡፡
4. አማላይ ሹመቶችና ጥቅማጥቅሞች፡- መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የትምህርት ሥርዓቱ ውጤት የሆነውን ኢንልጀንሺያ የስልጣንና የጥቅም ተጋሪ በማድረግ ከሙያዊ አገልግሎታቸው በማንሳት ሙያቸው ባልሆነ ሌላ ሙያ ላይ በማሰማራት ብቃት ያለውን ኢንተልጀንሺያ ሳይቀር ወደ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያነት ይቀይሩታል፡፡ በዚህም በሙያቸው ሊያገለግሉ ሲገባቸው በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ያለሙያቸው ተመድበው ወደ ሃሳዊ ኢንተልጀንሺያነት የወረዱ ዶክተሮችን፣ ፕፌሰሮችንና ባለሙያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምናልባትም ከኢንተልጀንሺያነት ወደምሁራንነት ሊያድጉ፣ ወይም ምሁራን ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶችን ሊያፈራ የሚችለውን ኢንተለጀንሺያ ወደ ሃሳዊ እንተሊጀንሺያነት ያወርዱታል፡፡
5. የጤናማ መድረኮች መመናመን፡- ምሁርነት በአንዴ የሚገኝ ምርት አይደለም፡፡ በበርካታ መድረኮች ታሽቶ የሚገኝ ነው፡፡ ስለሆነም ወጣት ምሩቃን አዳዲስ አስተሳሰቦችን አፍልቀው የሚያቀርቡባቸው መድረኮች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መድረኮች በዋናነት የመገናኛ ብዙሃን፣ የውይት መድረኮች ወዘተ. ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአገራችን እነዚህ መድረኮች አሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡ መድረኮቹ ቢኖሩም በብዛት በሃሳዊ ኢንተልጀንሺያዎች አሰልቺ ንግግርና በሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ካድሪዎች ቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው፡፡ እንኳን ምሁራንን ለማፍራት ሊያግዙ ቀርቶ የወጣቱን አስተሳሰብ ማበሽቀጥ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ መድረኮቹ የሃሳዊ ኢንተልጀንሻዎችና የሃይማኖታዊ ካድሬዎች ብቸኛ መፍንጫ ከመሆናቸው፣ ይልቅ ወደገንቢ መድረክነት እንዲቀየሩ ማድረግ ሃሳቡ ራሱ አስፈሪ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘመኑ ያመጣውን ማህበራዊ ሜዲያን መጠቀም እንኳን ክብረ ነክ የሆነ የጥላቻ፣ የስድብና የዘረኝነት ወረርሽን ሊያስከት የሚችል በመሆኑ ጉዳቱን የታዘበ ሰው ሳይቀር ከብሩን ላለማስደፈር ሲል አድፍጦ የሚሆነውን ይጠባበቃል፡፡
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በምሁራንና ኢነተልጀንሺያ ማፍራት ሂደት፡-
ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ሩብ ምእት አመት አስቆጠረ፡፡ በዚህ የ25 ዓመታት ጉዞው ዋናው ተልእኮው የሆነውን ዜጎችን አስተምሮ የማብቃት ተግባሩን ምን ያህል ተወጥቷል የሚለውን መመለስ በራሱ ምርምር የሚጥቅ ቢሆንም እንደ ዩኒቨርሲቲው አባልነቴ ልሰጠው የምችለው ምስክርነት ግን አዎንታዊ አይደለም፡፡ ከላይ የዘረዘርኳቸው ለምሁራን ድርቀት ምክንያት የሆኑትን ምክንያቶች ዲላ ዩኒቨርሲቲም እንተቋም ይጋራቸዋልናና፡፡ እነዚህን ችግሮች ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአቅሙ ለመቅረፍ በቀጣይ ጉዞው ቢያደርጋቸው የምላቸውን ነጥቦች ባጭሩ ብቻ ላስቀምጥ፡-
1. የትምህርትና ሥልጠና መስኮችን ዓለማቀፋዊ፣ አገራዊና አካባቢያዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ እና ብቁ ኢንተልጀንሺያ ማፍራት የሚያስችሉ አድርጎ መቅረጽ፤
2. ብቁ ኢንተልጀንሺያ ለማፍራት የሚያስችለውን ቁሳቁስ ለማሟላትና የሰው ኃይል ለመቅጠርና ይዞ ለማቆየት የሚበቃ ሀብት መፍጠር፤
3. የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች አዳዲስ አስተሳሰቦችን የሚያቀርቡባቸውን፣ የሃሳብ መለዋወጫና መንሸራሸሪያ ዕድሎችና መድረኮችን መፍጠር፤
4. እነዚህን ነገሮች ለማሟላት ከሁሉም በላይ ተቋማዊ ነጻነት ያሻልና፣ ነጻ ተቋም (Autonomous) ሆኖ የሚደራጅበትን አቅጣጫ አስቦ መንቀሳቀስ፡፡
ዋቢ
Feuer, Lewis (1976). What Is an Intellectual? In Aleksander Gella (ed.) The Intelligentsia and the Intellectuals. Beverly Hills: SAGE Publications Inc.
Sowell, Thomas (2012). Intellectuals and Society: Revised and expanded edition. Basic books.