02/04/2025
ካንስር ምንድን ነዉ? የካንሰር በሽታ የሚይዘዉ ማንን ነዉ?
[ ክፍል ፩ ]
እዉነተኛ የዕለት ከዕለት የዉሎ ገጠመኞች!
፩. ድንቡሽቡሽ ያለ የአራት አመት ልጇን በስስት እያሰበች 'ዶ/ር የልጄ ህመም ምንድን ነዉ? ንገረኝ 'የደም ካንሰር' ነዉ? ' እዉነት ነዉ? ' መረበሿ ይነበበኛል፤ ድንጋጤዋ ይታየኛል፤ ጭንቀቷ ይገባኛል፤ ህመሟ ይሰማኛል። እንባዎ ይገባኛል።
ስጋት አለ፤ ፍረሃት አለ፤ ጭንቀት አለ፤ ህመም አለ፤
ትጠይቀኛለች፤ አደምጣታለሁ። 'ካንሰር ግን ምንድን ነዉ?' 'ከሳምንት በፊት ይዘል ፡ ይጫወት፡ ይበላ ...ጤናማ የነበረ ልጄ ዛሬ የደም ካንሰር አለበት ስባል እንዴት ልመን?' ትጠይቀኛለች፤
በሀሳቤ የህክምና አማራጮችን እያሰብኩ ፤ ስለ ካንሰር ምንነትም ለማስረዳት ብዕሬን ከነጭ ወረቀት አገናኛለሁ።
፪. ከነገ ዛሬ ደረሰለኝ የሚሉትና ተስፋ የሚያደርጉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተማረ የሚገኘዉ የአይን ብሌኔ ልጃቸዉ የታፋ አጥንቱ (Femur) በማበጡ፡ አጥንት የሚሰብር ህመም እየተሰማ ሲያሰቸግረዉ ቀዬቸዉን ለቀዉ፣ መንገዱን አቋራርጠዉ ወደ እኛ ጋ ለመታከም መምጣታቸዉ ነበር፤ ለእብጠቱ የእግር ምራአይ (MRI) ፡ የበሽታዉን የመሰራጨት ሁኔታ ለማወቅም የሳምባ ሲቲ ስካን (Chest CT scan) አዘዝኩላቸዉ። ናሙና መወሰድም እንዳለበትም ቀስ በቀስ ለማሰረዳት ብሞክርም ንግግሬን አቆርጠዉኝ 'ልጄ ግን ይድናል? የመዳን ተስፋ አለዉ?' በተሸበረ ሰሜት ጠየቁኝ። ከቤተሰብ አንዱም 'ይኼ ነገር ካንሰር ነዉ እንዴ ? 'አለኝ።
፫. ሌሎችም በጣም ብዙ ህፃናትን እናክማለን። ቤተሰቦች በቀጠሮ የክትትል ቀናቸዉ የካንሰር ህክምናቸዉን ያጠናቀቁ ልጆቻቸዉን ይዘዉ ይመጣሉ። ልጆቹም ገና እንዳዩን ሮጠዉ ይጠመጠሙብናል። የቤተሰብ ደስታ....ፈገግታ! ቤተሰቦችም ያሳለፉት የነበረ የህክምና ጊዜን እያሰቡ 'ተመስገን' ሲሉ ይደመጠናል። በህክምና ላይ ላሉ ታካሚዎችና ለአዳዲስ የካንሰር ታካሚዎች ሞራልና ብርታት ይሆኗቸዋል። ከካንሰር ታክሞ መዳን እንደሚቻል ተምሳሌት ይሆናሉ።
ተስፍ አለ፤ መፍትሔ አለ፤ ህክምና አለ ፤ ታክሞ መዳን አለ።
∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞
ለመሆኑ ግን ካንሰር ምንድን ነዉ? የምንወዳቸው ሰዎች በካንሰር መታመማቸዉን ስንሰማ የሚሰማን ምንድን ነዉ? ወደ አዕምሯችን ቀድሞ የሚመጣዉ 'ተስፋ መቁረጥ' ወይንስ 'የህክምና አማራጮች?' ታሚሚዎችስ መታከምን ወይንስ መሞትን ያስባሉ? አብዛኛውን የካንሰር ህመም አይነቶች በጊዜ ከታወቁና ተገቢዉ ህክምና ከተደረገላቸዉ እንደሚድኑስ እናዉቃለን?
∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞
ሰዉነታችን የተገነባዉ መሰረታዊ የህይወት ትናንሽ ክፋዮች ከሆኑት ህዋሳት(cells) ነዉ። እነዚሀ ህዋሳት የራሳቸዉ የሆነ ጠባይና የስራ ድርሻ አለባቸዉ። ጤነኛ ህዋሳት ሲያረጁ ወይንም ጉዱት ሲገጥማቸዉ በሌላ ጤነኛ አዲስ ህዋሳት ይተካሉ፤ የተጓዳ ህዋስም ካለ እንዲስተካከል (repair ይደረጋል፤ ይኽም የጤነኛ ህዋሳት መገለጫቸዉ ነዉ።
ህዋሳት የተለመደዉን የጤነኛ ህዋሳት መንገድ መከተል ሲየቅታቸዉ የካንሰር ህመም ይከሰታል። የካንሰር ህዋሳት በሰዉነታቻን ዉስጥ ከቁጥጥር በላይ በሆነ መንገድ የሚራቡ (uncontrolled sustained proliferation) እና የማይሞቱ አዳዲስ ህዋሳትን (replicative immortality ) ፈጥረዉ ይተካሉ። እነዚህም የካንሰር ህዋሳት (cancer cells) እያደጉና እየተራቡ በመምጣት በጤነኛ ህዋሳት ላይ ግፊት በማሳደር (invasion) መጨናነቅን ይፈጥራሉ፤ የማያረጁና የማይሞቱ የካንሰር ህዋሳት (Resisting cell death) በሰዉነት ክፍላችን ይከማቻሉ። ለጤነኛ ህዋሳት የሚያስፈልጉ ንጥረ-ነገሮች፡ የደም አቅረቦት በመሻማት ጤነኛ ህዋሳት በአግባቡ ስራቸዉን ማከናዉን እንዳይችሉ ያደርጓቸዋል። የካንሰር ህዋሳት በጣም እየበዙ ሲሄዱ ወደ ሌሎች የሰዉነት ክፍል ሊሰራጩ (Metastasis) ተጨማሪ ምልክቶችን ይፈጥራሉ። ለምሳሌ የእግር የታፋ አጥንት ካንሰር (Femur Bone sarcoma) ወደ ሳንባ ተሰራጭቶ የትንፍሽ ማጠር ምልክት ፡ የሳምባ ሽፋን ዉኃ/አየር መቋጠር (Hydropneumothorax) ሊያመጣም ይችላል።
∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞
ካንሰር ዘር፣ ፆታ፣ ቀለም፡ የኑሮ አቅም ሳይለይ በሁሉም የዕድሜ ክልል ዉስጥ (ከህፃናት እስከ አዛዉንት) ያሉ የሚያጠቃ ህመም ነዉ። ካንሰር ከየትኛዉም የሰዉነት ክፍል ሊጀምር ይችላል። የካንሰር አይነቶች ስርጭትም በዕድሜና በፆታ የመለያያት እድል አለዉ። የካንሰር ህዋሳት በሰዉነታችን ዉስጥ የሚያድጉበት እና የሚሰራጩበት መንገድና ፍጥነት የተለያየ ነዉ፤ አንዳንደ የካንሰር አይነቶች በከፍተኛ ፍጥነት የማደግና የመሰራጨት ምልክት ያሳያሉ ፤ ሌሎች ደግሞ በዝግታ የማደገና የመሰራጨት አዝማሚያ ያሳያሉ። በአዋቂዎች ላይ የሳምባ ካንሰር፣ የጡት ካንሰር፣ የማህፀን ካንሰር፣ የአንጀት ካንስር፣ የፕሮስቴት ካንሰር ፣ ከጨጓራና ከገረሮ የሚነሱ ካንሰር ሊከሰቱ ይችላሉ። በህፃናትና በልጆች የሚከሰቱ ዋና ዋና የካንሰር አይነቶቸ በቅደም ተከተላቸዉ የደም ካንስር (Acute Leukemia)፣ የጭንቅላትና የህብለሰረሰር ዕጢዎች (Central Nervous Tumors)፣ የንፍፊት ዕጢ/ካንሰር(Lymphoma)፣ ኒዮሮብላስቶማ፣ የኩላሊት ካንሰር ፤ የአጥንት ካንሰር....ወ.ዘ.ተ ናቸዉ።
∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞
አብዛኞቹ የካንሰር አይነቶች እንደ እባጭ ያለ የሚያድ ዕጢ ይሰራሉ፤ ይሁንና ሁሉም ዕጢ/ዕባጭ ካንሰር ናቸዉ ማለት አይደለም። ካንሰር ያልሆኑ እጢዎች ምኝ ዕጢ (Benign tumor) ይበላሉ፤ የካንሰር ህዋሳትንና መገለጫዎችን የያዙ ዕጢዎች ከባድና አደገኛ እጢዎች (Malignant tumors) ይባላሉ። ምኝ ዕጢን ከከባድ አደገኛ እጢ ለመለየትም ከራዲዮሎጂ ምርመራ በተጨማሪ ናሙና ወስዶ እጢዉን መመርመር ያስፈልጋል።
ነገር ግን እንደ የደም ካንሰር (Leukemias) ያሉ የካንሰር ህመሞች በደም ህዋሳት አማካኝነት ወደ ተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች ይሰራጫሉ እንጂ እብጠት/እጢ አይሰሩም።
∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞∞
በቀጣይ ክፍል [ክፍል ፪] ካንሰር ከምን ይመጣል? የተለመዱ የካንሰር ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸዉ? የሚለዉን እናያለን።
በቸር ያቆዬን።
ዶ/ር ጋሻዉ አረጋ
የህፃናት ሕክምናና የልጆች ጤንነት ስፔሻሊስት
የደምና ተዛማጅ ህመሞች፤ የካንሰር ሰብ-ስፔሻሊስት