24/09/2022
ሄፓታይተስ ቢ በሄፐታይተስ ቢ ቫይረስ (HBV) የሚመጣ የጉበት ኢንፌክሽን ነው። ሄፓታይተስ ቢ ከአምስቱ የሄፓታይተስ ቫይረስ ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ሄፓታይተስ ኤ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ ናቸው። እያንዳንዳቸው የተለያየ አይነት ቫይረስ ናቸው። በተለይም ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ የሚባለው የበሽታው ዓይነት ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ ተደብቆ ህይወት ሊቀጥፍ የሚችል በመሆኑ ድምፅ አልባው ገዳይ በሽታ ይባላል። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ምንጭ፣ በዓለም ዙሪያ ወደ 296 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሄፐታይተስ ቢ ይያዛሉ። ሄፓታይተስ ቢ በየአመቱ ቢያንስ 600ሺ ሰዎችን ይገድላል።
ሄፓታይተስ ቢ የተለያዩ የጉበት ሴሎችን በመጉዳት ወደ ካንሰርነት የሚቀየር በሽታ ነው። የ ሄፓታይተስ ኢንፌክሽን አጣዳፊ ወይም ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል። አጣዳፊ የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች በአዋቂዎች ላይ በፍጥነት እንዲታዩ ያደርጋል። በወሊድ ጊዜ ጨቅላ ህጻናትን አጣዳፊ ሄፓታይተስ ቢን ቀስበቀስ ያዳብራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሄፓታይተስ ምልክቶች አይታዩም።በወቅቱ የሚደረገው የጉበት ምርመራ እንኳ በሽታውን ላይለይ ይችላል። ለዚህም ነው ድምፅ አልባው ገዳይ በሽታ የሚባለው።
♦️የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች ምንድ ናቸው?
የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች ለወራት ላይታዩ ይችላሉ።ነገር ግን የተለመዱ ምልክቶች
➣ ድካም
➣ጥቁር ሽንት
➣የመገጣጠሚያ እና የጡንቻ ህመም
➣የምግብ ፍላጎት ማጣት
➣ ትኩሳት
➣የሆድ ውስጥ ህመም ወይም ምቾት ማጣት
➣ድክመት
➣የአይን ነጩ ክፍል እና የቆዳ ቢጫ መሆን
ማንኛውም የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች ከታዩ አስቸኳይ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ከ 60 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ደግሞ እነዚህ የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች በጣም የከፉ ይሆናሉ። በሄፐታይተስ ቢ ከተያዛችሁ ወዲያውኑ ህክምና አድርጉ። ምክንያቱም ኢንፌክሽኑን መከላከል ትችላላችሁ።
♦️ለሄፐታይተስ ቢ መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች ምንድናቸው ?
ሄፓታይተስ ቢ በደም ወይም በሌሎች የሰውነት ፈሳሾች፣ የዘር ፈሳሽ ወይም የሴት ብልት ፈሳሾችን ጨምሮ የሚተላለፍ የቫይረስ ኢንፌክሽን ነው። ሄፓታይተስ ቢን ከሚተላለፉባቸው መንገዶች መካከል፡-
➣ኮንዶም ወይም ሌላ መከላከያ ዘዴዎችን ሳይጠቀሙ ይህ ቫይረስ ካለበት ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ
➣ ለደም የተጋለጡ የጥርስ ብሩሾችን፣ ምላጭን ወይም የጥፍር መቁረጫዎችን መጋራት
➣ባልፀዳ ወይም (sterilized) ባልሆነ መሳሪያ መነቀስ ወይም አካልን መበሳት
➣ አደንዛዥ እጾችን በመርፌ መወጋት እና መርፌዎችን ወይም ሌሎች መሳሪያዎችን መጋራት
➣በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል። ♦️ሌላው ምንም እንኳን ቫይረሱ በምራቅ ውስጥ ሊገኝ ቢችልም, ሄፓታይተስ ቢ በሚከተሉት መንገዶች አይተላለፍም. እነዚህም
➣መሳሳም
➣ማስነጠስ ወይንም ደግሞ ማሳል ዕቃዎችን መጋራት አይተላለፍም።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በይበልጥ ለሄፓታይተስ ቢ የመያዝ ወይም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። እነዚህም ሰዎች ➣የጤና ባለሙያዎች
➣ መርፌ መድሃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች
➣ሄፓታይተስ ቢ ካለባቸው ወላጆች የተወለዱ ሕፃናት
➣ሄፓታይተስ ቢ ያለባቸው የወሲብ አጋር ያላቸው ሰዎች ➣የኩላሊት እጥበት(dialysis ) የሚወስዱ ሰዎች
ከሌሎች ሰዎች በይበልጥ ለሄፓታይተስ ቢ በሽታ ተጋላጭ ናቸው።
♦️ ሄፐታይተስ ቢን እንዴት መከላከል ይቻላል ?
ሄፓታይተስን በሁለት መንገድ መከላከል ይቻላል። የመጀመሪያው በተፈጥሮአዊ መንገድ ሰውነታችን በራሱ antibody በማመንጨት በሽታውን ሲከላከልልን በዚህ መንገድ ከበሽታው የዳኑ ሰዎች ቫይረሱ ከሰውነታቸው ከጠፋ በድጋሜ ለበሽታው አይጋለጡም። ሁለተኛው ደግሞ
የሄፐታይተስ ቢ ኢንፌክሽንን ለመከላከል በጣም ጥሩው መንገድ የሄፐታይተስ ቢን ክትባት መውሰድ ነው። ክትባቱ በጣም አስተማማኝ እና ውጤታማ ነው።
➣ ሁሉም ሕፃናት, በተወለዱ በ 24 ሰዓታት ውስጥ ክትባቱን ማግኘት ይኖርባቸዋል። ሌላው
➣በወሊድ ጊዜ ያልተከተቡ ልጆች እና አዋቂዎች
➣ ከ19 እስከ 59 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ያልተከተቡ አዋቂዎች
➣ እድሜያቸው 60 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ጎልማሶች የሄፐታይተስ ቢ ክትባቱን ማግኘት ይኖርባቸዋል።
የሄፐታይተስ ቢ ክትባቱ ብዙውን ጊዜ በሶስት ክትባቶች ይሰጣል። ይህም የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠ በኋላ ሁለተኛው ከ 1 ወር እና ከ 6 ወር በኋላ ይሰጣል። ሦስተኛው ክትባት ደግሞ በ 1 ወር ልዩነት በሁለት መጠን ይጠናቀቃል።
♦️ሄፓታይተስ ቢ ተላላፊ ነው?
ሄፓታይተስ ቢ በጣም ተላላፊ ነው። ከደም እና ከሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር በመገናኘት ይተላለፋል። ምንም እንኳን ቫይረሱ በምራቅ ውስጥ ሊገኝ ቢችልም በመሳም አይተላለፍም።በተጨማሪም በማስነጠስ፣ በማሳል ወይም በጡት ማጥባት አይተላለፍም።
♦️በሄፓታይተስ ቢ ከተያዛችሁ በኋላ ለ 3 ወራት ያህል የሄፐታይተስ ቢ ምልክቶች ላይታዩ ይችላሉ። ምልክቶቹ ለብዙ ሳምንታት ሊቆዩ ይችላሉ። ነገር ግን ምንም ምልክቶች ባታዩም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ይተላለፋል። ቫይረሱ ከሰውነት ውጭ ሊኖር ይችላል እና ቢያንስ ለ7 ቀናት ተላላፊ ሆኖ ይቆያል ።