16/09/2023
በምግብ ወይም በባአድ ነገር መታነቅ
በጣም ከሚወዱት ወይም እንበል ከቅርብ ጓደኛዎ ጋር ኖት፡፡ ጥሬ ሰጋ መብላት አማሮት፡፡ እናም አልቀረም፡፡ አስቆርጣችሁ መብላት ጀመራችሁ፡፡ ድንገት አንድ ሁለቴ እንደጎረሳችሁ ጓደኛችሁ በስጋ ታነቀ፣ አንገቱንም ይዞ ወዲህ ወዲያ ማለት ጀመረ፡፡ ለመሆኑ የሚወዱትን ጓደኛዎን ህይወት ለመታደግ ምን ያደርጋሉ
በምግብ ወይም በባአድ ነገር መታነቅ የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚቀማ አደጋ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ አደጋውን ለመከላከልም ሆነ የደረሰውን አደጋ መፍትሔ ለመስጠት እጅግ ቀላል መሆኑ ነው፡፡
እርሶ ይህን ህይወት የመታደግ ክህሎት ለማወቅ ዝግጁ ኖት
በላይኛው የመተንፈሻ አካል ማለትም በጉሮሮ ውስጥ ምግብ ወይም ሌሎች ባዕድ ነገሮች ሲገባና የተጎጂው የመተንፈሻ አካል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመዝጋት የመተንፈስ ችግር ሲያስከትል መታነቅ (choking) ደረሰበት ይባላል፡፡
የመታነቅ ደረጃ፡- መታነቅ በሁለት ይከፈላል ሙሉ በሙሉና በከፊል መታነቅ
በከፊል መታነቅ ምልክቶች የተቆራጠ ቃለትን መናገር፣በትንሹ መተንፈስ እንዲሁም ከፍተኛ ሳል መሳል ናቸው፡፡
ልናደርግ የሚገባን የመጀመሪያ እርዳታም
1. በተቻለ መጠን በመደጋገም እንዲያስል ማበረታታት፡፡
2. ያነቀው ምግብ ወይም ባእድ ነገር ሙሉ በሙሉ መውጣቱንና ተጎጂው ህሊናውን ወይም ራሱን በደንብ የሚያውቅ መሆኑን ሳያረጋግጡ ምንም ነገር ፈሳሽ ጭምር በአፍ መስጠት አይገባም፡፡
3. ተጎጂው ማሳል እና መተንፈስ ካቃተው ተጎጂው ሙሉ በሙሉ ታንቋል ማለት ስለሚሆን ቀጣዩን እርዳታ ይስጡ፤ እርዳታ እየሰጡ አምቡላንስ ይጥሩ፡፡
ሙሉ በሙሉ ሲሆን ተጎጂው መተንፈስ፣መናገር፣ወይም መሳል አይችልም፡፡ ስለሆነም አንገቱን በሁለት እጆቹ ጥርቅም አድርጎ በመያዝ እርዳታ ፍለጋ ራሱን ሲያንቀሳቅስ ይታያል፡፡
ይህ ምልክት ሲያጋጥም የአየር ቧንቧው ሙሉ በሙሉ የተዘጋ መሆኑን ተረድተን በሚከተለው መንገድ ለመርዳት መሞከር ይኖርብናል፡፡
የእርዳታ ጥሪ ማድረግ
ባእድ ነገር ወደ ጉሮሮዉ ገብቶ የታነቀን ሰው አፉን በማስከፈት ባዕድ ነገሩ የሚታይ ከሆነ ብቻ ጣቶችን አስገብቶ ለማውጣት መሞከር፤
ያነቀው ነገር የማይታይ ከሆነ የታነቀውን ሰው በማስጎንበስ በሁለቱ ብራኳ አጥንቶች መካከል ፈጠን ብለን ለ5 ጊዜ ብንመታው የገባው ነገር ሊወጣ ይችላል፤
በዚህ እርዳታ መዉጣት ካልቻለ ከተጎጂዉ በስተጀርባዉ በመቆም አንደኛዉን እጅ በመጨበጥ፤ ሌላኛዉን እጅ በላዩ ላይ በመደረብ በተጎጂዉ እንብርትና ከታችኛዉ ደረት መካከል አድርገን ወደ ዉስጥና ወደ ላይ በተከታታይ በመጫን መርዳትና በየመሀከሉ መዉጣቱን መመልከት፤
በድንገት እራሱን ከሳተ በቀስታ በጀርባዉ ማስተኛትና ደረቱን ቢያንስ በደቂቃ መቶ ጊዜ ያህል በመደጋገም በመጫን የደም ዝዉዉሩንና አተነፋፈሱን ማገዝ፤
ይህን ዓይነቱን አደጋ እንዴት ቀድመን መከላከል ይቻላል
• በተለይ ከ4ዓመት በታች ህፃናት ያገኙትን ነገር ወደ አፋቸው ስለሚወስዱ ሀፃናት በሚጫወቱበት እና በሚገኙበት አካባቢ እንደ ጥራጥሬ፤ ሳንቲም፤ ቁልፍ፤ ብሎን ፍራፍሬ እና የመሳሰሉት እንዳይኖር ማድረግ በመጫዎቻነትም አለመሰጠት
• በህፃናት አመጋገብ ዙርያ ጥንቃቄ ማድረግ፡፡ በደንብ የላመ ምግብ መመገብ፤
• በጨዋታ ጊዜ በአፋቸው የሚበላ ነገር ይዘው መሯሯጥ መከልከል
• ሕጻናት በሚመገቡበት ጊዜ ብቻቸውን አለመተው
• ማንኛውም ሰው ምግብ በሚመገብበት ጊዜ በደንብ አኝኮ መዋጥ አለበት፡፡ በተለይ ጥሬ ስጋና አትክልት በደንብ ካልታኘኩና በትንሹ ካልተቆራረጡ የተወሰነ ጫፍ በጥርስ ላይ ተጣብቆ ሲቀር ሌላው ጫፍ በጉሮሮ አከባቢ ሲደርስ ወደ ታችአንዳይወርድ በመያዝ መታነቅን ያስከትላል
• እያወሩ እና እየሳቁ መመገብ ለመታነቅ ይዳርጋል