24/04/2026
ተቀጥራችሁ የምትሰሩ ሰራተኞች ሁሉ ልታውቁት የሚገባ
: አዲስ የሰበር አቋም!
🔑🔑🔑🔑🔑
ለ5 ተከታታይ ቀናት ያለፈቃድ ከስራ የቀረ ሰራተኛ
ያለማስጠንቀቂያ ከስራ መሰናበት ያለበት ስለመሆኑ
በ7 ዳኞች የተሰጠ ትርጉም!
1. ሰበር በ7 ዳኞች መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በሰ/መ/ቁ 271726 የተሰጠው አስገዳጅ ትርጉም ከዚህ በፊት በሰ/መ/ቁ 249795 ሰራተኛው ለተከታታይ 5 ቀናት ቢቀር እንኳን ከስራ ለቀረበት ለእያንዳንዱ ቀን አሰሪ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የስራ ውልን ማቋረጥ እንደማይችል ተይዞ የነበረውን የሰበር አቋም የቀየረ ብሎም በሰራተኞች የስራ ደህንነት ላይ አሉታዊ ውጤት የሚኖረው ነው፡፡
2. ሰበር በ7 ዳኞቹ በያዘው አዲስ አቋሙ ሰራተኛ ያለፈቃድ ለ5 ተከታታይ ቀን ከቀረ ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበትን የሚፈቅድ ይዘት በአዋጅ 1156 ላይ የለም ብሏል ፡፡
3. ይህ አዲስ አቋም የአንቀጽ 27 (1)(ለ) ይዘት በዚህ አዋጅ ከተመለከቱ እረፍቶችና ልዩ ልዩ ፈቃዶች ውጭ የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ ለ5 ቀናት ከስራ መቅረት ለአሰሪው የስራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ ያስችለዋል የሚል ነው።
ነገር ግን የዚህ አንቀፅ ይዘት በግልፅ የሚያመለክተው አሰሪው የሰራተኛውን ከስራ መቅረት ለስራ ስንብት መነሻ ሊያደርግ የሚችለው ሰራተኛውን ለማረም የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ስለመሆኑ ብቻ ነው።
ከዚህ አንጻር የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ ሳይደርሰው ከስራ ቀርቷል በሚል የስራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት የህግ መሰረት አለ ወይ? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡
4. የሰበር ሰሚ ችሎቱ በ7 ዳኞች አዲስ ለሰጠው አስገዳጅ ትርጉም መነሻ ያደረጋቸው አመክንዮዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
4.1. በአንቀጽ 27 (1)(ለ) ሰራተኛው በተከታታይ ለ5 ቀናትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ፈቃድም ሆነ እረፍት ሳይሰጠው ከስራ ቢቀር አሰሪው የስራ ውሉን ያለ ማስጠንቀቂያ ከማቋረጡ በፊት ለሰራተኛው የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ስለመሆኑ አይደነገግም፡፡ (የ7 ዳኞች አዲስ አቋም)
4.2. በአዋጁ አንቀጽ 27(1)(2) ላይ የተመለከተው የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ ሰራተኛው ያለፈቃድ ከስራ ከቀረ በኋላ ወደ ስራው ሲመጣ ለወደፊት ተመሳሳይ ጥፋት እንዳፈጽም ተገልጾ የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ እንደመሆኑ መጠን ለ5 እና ተከታታይ ያለ ፈቃድ ለቀረ ሰራተኛ ጥፋቱን እንዳይደግም በመግለጽ ሰራተኛው ከስራ ለቀረበት ለእያንዳንዱ ቀን በአንቀጽ (27)(1)(ለ) ላይ የተመለከተውን ማስጠንቀቂያ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡
ለዚህ ድምዳሜ ምክንያት በሚል የተሰጠው ደሞ ሰራተኛው ከ5 ተከታታይ ቀናት በላይ ከቀረ በኋላ ሰራተኛውን አግኝቶ ያለፈቃድ ከስራ ከመቅረት ጥፋቱ እንዲታረም አስሪው የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት አሰሪው እድል ሊያገኝ አይችልምና የሚል ነው፡፡
4.3. ከዚህም ባሻገር የጥፋት ተግባሩን እየቀጠለ ያለንና ገና ወደ ስራ ገበታው ያልተመለሰን ሰራተኛን ጥፋቱን እንዳይደግም ወይም ለወደፊቱ ከጥፋቱ እንዲታረም ተገልጾ የጽኁፍ ማስጠንቀቂያ (Warning in writing) እንዲሰጠው አሰሪውን ማስገደድ ከስረ አመክንዩ (logic) አኳያ ሲታይም አሳማኝነት ያለው አይደለም፡፤ የሚቻል አይደለም የሚለውን ነጥብ አንስተዋል፡፡
4.4. በተጨማሪም ለተከታታይ 5 ቀናት ያለ በቂ ምክንያት ከስራ መቅረት ሌላ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይኖር አሰሪው ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውልን እንዲያቋርጥ የሚያስችለው ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከመታወጁ በፊት በስራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1)(ለ) በግልጽ ተደንግጎ የሚገኝ ነው አዋጅ 1156/2011 ለ5 ተከታታይ የስራ ቀናት ስለቀረ ሰራተኛ ሊኖው ስለሚገባ ውጤት ምንም አይልም የሚለውንም አንስተዋል፡፡
4.5. በሌላ በኩል ህጉ ግልጽነት ሲጎድለው ጠቅላላን የህጉን ይዘትና አቀራረጽ መሰረት በማድረግ ክፍተቱን በትርጉም መሙላት አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተው፡፡ የአዋጅ 1156 አንዱ አላማ አሰሪና ሰራተኛ የጋራ ራእይ ኖሯቸው ለድርጅቱ ምርታማነት እንዲሰሩ ስለመሆኑ ሰራተኛ የስራ ሰአትና የስራ ዲሲፒሊን አክብሮ ስራውን የመሰይሰራ ከሆነ አሰሪው ተወዳዳሪ ሊሆን አይችልም የሚለውም ለአዲሱ የ7 ዳኞች የሰበር አቋም ሌላ መነሻ ሆኗል፡፡
4.6. በመጨረሻም ሰበር የ1156ን የረቂቅ ህጉን አጭር ማብራሪያና ሀተታ ዘምክንያት ለአዲስ አቋሙ መነሻ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
5. እነኚህን ከላይ የተመለከቱትን ምክንያቶችን በመዘርዘር በሰ/መ/ቁ 249795 ሰበር ይዞት የነበረውን ሰራተኛው በተከታታይ ከ5 ቀናት በላይ ለሆነ ጊዜ ቢቀር እንኳን አሰሪው ሰራተኛው ከስራ ለቀረበት ለእያንዳንዱ ቀን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የስራ ውልን ማቋረጥ እንደማይችል ሰጥቶ የነበረውን አስገዳጅ ትርጉም ለውጦ በ7 ዳኞች መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በሰ/መ/ቁ 271726 በሰጠው አዲስ አስገዳጅ ትርጉም መሰረት የአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27/1/ለ ድንጋጌ ሰራተኛው በዚሁ አዋጅ ከተመለከቱ እረፍቶችና ልዩ ልዩ ፈቃዶች ውጪ ለአምስት ተከታታይ የስራ ቀናትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ከስራ ላይ ከቀረ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልግ የስራው ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ይችላል የሚል አቋም ወስዷል፡፡
ስለሆነም ሰራተኞች ይህን አዲስ የሰበር 7 ዳኞች አስገዳጅ ትርጉም መገንዘብና መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል።
Legal Eagles Law Firm LLP Seble Asefa #ጠበቃ #ሕግምክር #ጠበቃሰብለአሰፋ