11/10/2025
ስታቲን (statin) የልብዎት የደህንነት ቀበቶ ነው - ካልታሰበ የልብ አደጋ የሚከላከል።
ሁሌም መኪና ስንነዳ ወይም ስንሳፈር የደህንነት የመቀመጫ ቀበቶ ማሰር ይገባል አይደል? ይህን የምናደርገው መንገዱ ሳይመች ሲቀር ወይም ገደል አፋፍ ስንደርስ ብቻ ሳይሆን ከስንት አንዴም ቢሆን ድንገት አደጋ ቢከሰት ህይወታችንን ይታደገናል ብለን ነው።
ስታቲን የሚባለው የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒትም የሚረዳው እንዲሁ ነው፤ ወደፊት ድንገት ሳናስበው ሊከሰት የሚችል የልብ ድካም ወይም ስትሮክ እንዲታደገን ነው።
ስታቲን የምንወስደው የአጭር ጊዜ ጤና መሻሻል ጠብቀን ሳይሆን ሳይጠበቅ ከሚመጣ የማይታይ የደም ስር ችግር ለመከላከል ነው። ስታቲን መድሃኒት ስራዉን ሲሰራ እንደመኪና ላይ የደህንነት ቀበቶ ነው ያልነው ለዚህ ነው።
የልብ እና ተያያዥ የደም ስር ህመሞች (cardiovascular disease) የአለማችን ቁጥር አንድ ገዳይ በሽታ ነው። ለዚህ የልብና የደም ስር ህመም ዋነኛው አጋላጭ መንስኤ ደግሞ በደም ውስጥ ከፍ ያለ ኮሌስትሮል ነው። እንደስታቲን ያሉ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች የልብ እና ተያያዥ የደም ስር በሽታዎችን በእጅጉ እንደሚቀንሱም በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል።
ስታቲኖች ጎጂ ኮሌስትሮልን ከመቀነስ ባለፈ በበርካታ መንገዶች የደም ስር ጤናን ይጠብቃሉ። የልብ ድካምንን እና ሌሎችንም ስር የሰደዱ የደም ስር ህመሞች ከ25 እስከ 40 በመቶ ያህል ይቀንሳሉ።
ስለሆነም የልብ ህመም ላለባቸው ወይም ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው (ለምሳሌ ስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ በዘር የሚመጣ የኮሌስትሮል ችግር ወዘተ) ሰዎች ይታዘዛሉ።
እርግጥ ነው ስታቲን ስለምወስድ ብለን እንደፈለግን ሁሉን ሳንመርጥ ለመብላት አይደለም። ሁሉም መድሃኒቶች ከጤናማ አመጋገብና አካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር መደመር አለባቸው።
ማጠቃለያ
ስታቲን ያስፈልገወታል ተብለው በሃኪም ከታዘዘለዎት በአግባቡ ይውሰዱ። ስታቲን የልብዎት የደህንነት ቀበቶ ነው - ካልታሰበ የልብ አደጋ የሚከላልከል።
የዚህን ጽሁፍ ሙሉ መረጃ ቲክቶክ ላይ በዚህ ሊንክ ይመልከቱ፤ ለሌሎችም ያጋሩ!
Rf-Dr Melaku (Endocronologist)
Check out Dr. Melaku Taye’s video.