07/04/2025
የጤና ባለሞያዎች ችግር በቶሎ ካልተፈታ የጤና ስርዓቱ አደጋ ውስጥ ይገባል ሲል የትግራይ የጤና ባለሞያዎች ማህበር አስታወቀ
ማህበሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ችግር በቶሎ መፍትሄ ካልተሰጠውና ተገቢውን ተኩረት ካላገኘ ሰራተኞቹ ስራ እየለቀቁ መሄዳቸው አይቀሬ ነው ያለ ሲሆን ይህ ደግሞ በማገገም ላይ የሚገኘውን የጤና ስርዓት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሏል።
ማህበሩ አሁን ላይ እየሰራቸው ስላሉ ስራዎችና እየገጠሙት ስለሚገኙት ችገሮች ለሚመለከታቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና ለፌደራል መንግስት አመራሮች አቅርቧል ያሉት የትግራይ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ሊቀመንበሩ ዶ/ር ፍስሀ አሸብር ከችግሮቹ መካከል ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝ፣ የሙያተኛ ከለለ አለማግኘት ፣ የትራንስፖር አገልግሎት፣ የስራ ቦታ፣ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ፣ ነፃ የህክምና አገልግሎት፣ በኮቪድ ጊዜ ለተሰራ ስራ ያልተፈፀመ ክፍያና የደመወዝና የስራ መደብ እርከን እድገት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ሊቀመንበሩ አክለው ሞያተኛው ያለውን ሁሉ ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሞያተኛው እያበረከተው ላለው አስተዋፅኦና እየከፈለው ላለው ዋጋ ተገቢ ክብርና እውቅና ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።
ማህበሩ አሁንም እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምንም ምላሽ ሳያጉኙ አመት ከስምንት ወር መቆየታቸው የገለፁት ዶ/ር ፍስሃ የሞያተኛው ጥያቄና ችግር በአፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት የትግራይን የጤና ስርዓት አደጋ ውስጥ የሚከት ይሆናል፣ ሞያተኛውም በዚህ ተስፋ በመቁረጥ ስራ እየለቀቀ ይሄዳል ሲሉ መናገራቸውን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።
ከዚህ ቀደም ማህበሩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ከሰሜኑ ግጭት ወዲህ 200 ዶክተሮች ጨምሮ ከ915 የህክምና ባለሞያዎች ከስራ ለቀው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ወደ ውጭ ሀገራት መሰደዳቸው መግለፁ አይዘነጋም።