15/11/2025
የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሕፃናት ዙሪያ ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተጠቆመ
አርባ ምንጭ፡- ህዳር 6/2018 ዓ.ም ( የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ)
በጋሞ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አዘጋጅነት "ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ቃል የነጭ ሪቫን ቀንና የሕፃናት ቀን በድምቀት ተከብሯል።
የጋሞ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሕሩት ማሞ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለፁት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በቅርብ ሰዎች ጭምር የሚፈፀሙ መሆናቸው ጉዳዩ ውስብስብ እና አሳሳቢ እንደሚያደርግ ገልፀው የአለም አቀፍ ትኩረት አግኝተው የወረዱ የንቅናቄ መድረኮችን በዓላማ ጽናት መፈጸም ይገባል ብለዋል።
በሴቶችና ሕፃናት ደህንነት የወጡ ደንቦች፣ ህጎችና ፖሊሲዎች በአግባቡ እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ አካላት የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራ ጠቁመው በፍትህ ተቋማት የተያዙ የወንጀል ጉዳዮች በወቅቱ እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል።
የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ዋናቃ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ የስነልቦና፣ የአካል፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ጥቃት መከላከል የሁሉ ባለድርሻ አካላት መሆኑን ገልፀው በታችኛው መዋቅር የሚስተዋለውን የጉዳዩን አሳሳቢነት ማቃለልና ከመረጃ ማጥፋት ተግባር እንዲቆጠቡ አስገንዝበዋል።
በጤናው ዘርፍ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ካንሰር እና የስነ ተወልዶ ጤና ፓኬጆችን ለመተግበር የሴቶች ልማት ሕብረቶች ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል ።
የጋሞ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ምሕረት ኩንታ በበኩላቸው በጋራ ከሚሰሩ ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር የስተሪንግ ኮሚቴ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርግት አስወጋጅ ኮሚቴና የፍትህ ፎረም ማቀናጀት እንደሚገባ አውስተው የሕፃናት ጊዜያዊ መቆያ ማዕከላት ግንባታና የጥበቃ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በሕፃናት ጥቃትና ሕገወጥ ዝውውር የመከላከል ተግባርና ሕፃናት በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹና የሚደመጡ እንዲሁኑ ስሰራ መቆየቱን የገለፁት ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ አከባቢዎች ለስራ በሚል የሚመጡ አካላት ማንነታቸው እንዲጣራ በአጽንኦት ጠይቀዋል።
በመጨረሻም ጥያቄና መልስ ውድድር በማካሄድ እና በሰቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን በማውገዝ መድረኩ ተጠናቋል።