21/11/2025
በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የማህጸን መንሸራተት ነጻ የህክምና አግልግሎት በዘመቻ እየተሰጠ መሆኑን የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ባለሙያ ወ/ሮ ወርቅነሽ አሰጌ በዘመቻ መርሃ ግብሩ እንዳሉት፥ የማህጸን መውጣት በአንዳንድ እናቶች ላይ የሚታይ የጤና ችግር ነው።
በሽታውን ለማከም ከፍተኛ የሙያተኛ አቅም እና ግብዓቶች የመጠይቅ እንደሆነ የጠቁሙት ባለሙያዋ
ቢሮው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከዊንግስ ኦፍ ሂሊንግ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ዘመቻውን እያካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በመጀመሪያ ዙር 15 የዘመቻ ቀናት ከ60 በላይ እናቶችን በሆስፒታሉ ማከም መቻሉን የገለጹት ወ/ሮ ወርቅነሽ ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ከአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ችግሩ አሳሳቢ ነው ያሉት ወ/ሮ ወርቅነሽ በቀጣይም በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህጸንና ጽንስ ህክምና ስፔሻለስት ዶ/ር አለሙ ተሻለም፤ የማህጸን መውጣት በስፋት በወልድ ወቅት በእናቶች ላይ የሚከሰት መሆኑን አብራርተዋል።
ከፍተኛ ህመምን የሚያስከትል መሆኑንም ጠቅሰው ከግንዛቤ እጦት የተነሳ ለረጅም ጊዜ ብዙዎቹ በህመሙ እንደሚሰቃዩ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮው ያቀረበላቸውን ጥሪ ተከትሎ በመርሀ ግብሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እናቶችን በጥንቃቄ በማከም ጤንነታቸውን መመለስ መቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡
የዊንግ ኦፍ ሂሊንግ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስተባባሪ ዶ/ር ቃልኪዳን ይታየው በበኩላቸው የማህጸን መንሸራተት የደረሰባቸው እናቶች ህክምና አግልግሎቱን አገኝተው ሙሉ ጤንነታቸው እንድመለስ ከመስራት ባለፈው በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚደረግ የዘመቻ መርሀ ግብር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ያለአቻ ጋብቻ እና የተለያዩ የስራ ጫናዎች የማህጸን መንሸራተትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉም የሚናገሩት ዶ/ር ቃልኪዳን ሽንት እና ሰገራን ያለመቆጣጠር፣ በዳሌ እና በወገብ አከባቢ ከፍተኛ የህመም ስሜት መኖር ከበሽታው ምልክቶች መካከል እንደሚጠቀሱም አሳውቀዋል፡፡
የህክምና አግልግሎቱን የሚያገኙ እናቶችም ህመሙ እስኪሻላቸው ድረስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመው ሌሎችም ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት በመምጣት የአግልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የበሽታው ህመም እጅግ ከባድ እና ቤተሰብን እስከመበተን የሚያደርስ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ህክምናውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ታካሚዎችና የታካሚ ቤተሰቦች ናቸው ፡፡
ታካሚዎቹ ለተመቻቸላቸው ነጻ የህክምና አግልግሎትም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን የቤንሻንጉል ሚድያ ዘገባ ያመላክታል።