08/11/2024
በደብረታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሊቋቋም የታሰበውን የጡት ካንሰር ህክምና መስጫ ማእከል እውን ለማድረግ ሁሉም አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ!
ዓለም አቀፉን የጡት ካንሰር ቀን አስመልክቶ በደብረታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከበሽታው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እና በሆስፒታሉ የጡት ካንሰር ህክምና ማእከልን ማቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የሆስፒታሉ፣ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደርና የደቡብ ጎንደር ዞን የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይቱ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የደብረታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሰውመሆን ደሳለኝ እንደተናገሩት የጡት ካንሰር በሽታ በርካታ ወገኖችን ለህመምና ለሞት እየዳረገ የሚገኝ አስከፊ በሽታ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በበሽታው የሚያዙ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ስለ በሽታው የጠራ ግንዛቤ በመያዝ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸውም አስገንዝበው በሆስፒታሉ የፊታችን ሰኞ ጀምሮ የጡት ካንሰር ልየታ ስራ የሚጀመር ስለሆነ እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ ሴቶች ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡
ዶክተር ሰውመሆን አያይዘውም በሆስፒታሉ የጡት ካንሰር ህክምና መስጫ ማእከል ለማቋቋም በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ማእከሉን ለማቋቋም የሚመለከተቸው የመንግስት አካላት እና መንግስታና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ስለ ጡት ካንሰር ምንነት፣ አጋላጭ ምክንያቶች፣ የበሽታው ምልክቶች፣ የምርመራ መንገዶች፣ የበሽታው ደረጃዎች፣ የህክምና ዘዴዎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በዘርፉ ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የጡት ካንሰር በሽታ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር ለማስቀረት ለማህበረሰቡ ስለ በሽታው በተገቢው ሁኔታ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ሴቶች በሚፈለገው እድሜ ላይ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ የጡት ካንሰር ህክምና ማእከልን በማቋቋም አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የተያዘው እቅድ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ተናግረው ስራውን በቀላሉ በማሰጀመር ሊያግዙና ሊደግፉ የሚችሉ አካላትን ማስተባበር እንደሚያስፈልግም ጠቁመው ለህክምና ማእከሉ እውን መሆን ማህበረሰቡና ሌላውም አካል ሊሰራና ሊተባበር ይገባልም ብለዋል፡፡