29/09/2022
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም
/Sudden cardiac arrest/ ምንድነው ?
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም /sudden cardiac arrest/ ልብ በድንገት ምቱን በሚያቆምበት ጊዜ የሚከሰት ነው።
ይህ ወዲያውኑ መታከም ያለበት የሕክምና ድንገተኛ አደጋ ሲሆን ወዲያውኑ የማይታከም ከሆነ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ብዙ ሰዎች ላይ ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡ልብ በመደበኛ ምት ውስጥ እንዲመታ የሚያደርግ አብሮ የተሰራ የኤሌክትሪክ ስርዓት አለው።
በ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ግዜ በኤሌክትሪክ ስርዓቱ ላይ ችግር ይከሰታል ይህም ወደ ያልተለመደ የልብ ምት ይመራዋል።
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ውስጥ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ያልተለመደ የልብ ምት ክስተት የልብ በሀይል መርገብገብ ወይም “ventricular fibrillation” ይባላል በዚህ ምት ውስጥ ፣ የልብ የታችኛው ክፍሎች (ventricles) በመርገብገብ በቂ ደም ለሰውነታችን መስጠት አይችሉም በዚህም ምክንያት የሰውነታችን ዋና ዋና ክፍሎች በቂ ደም ባለማግኘት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በምን ይከሰታል?
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም የቀደመ የታወቀ የልብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ይሁን ያልታወቀ ሰዎች ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ሊያስከትሉ የሚችሉ የልብ ችግሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
1. Coronary heart disease /heart attack/ - ደም ወደ ልብ የሚያመጡ የደም ቧንቧዎች በስብ ሲዘጉ የሚከሰት ነው
2.Cardiomyopathy - በተለያየ ምክንያት የሚመጡ የልብ ጡንቻ ችግሮች
3. Arrhythmia - በልብ ኤሌክትሪክ ስርዓት ላይ ያሉ ችግሮች የልብ ምት መዛባት ሲያመጡ የሚከሰት ነው
4.Heart failure /የልብ ድካም/ - ይህ ማለት ልብ በበቂ ሁኔታ ደም ለሰውነታችን መስጠት አለመቻል ነው፡፡
ሌሎች ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
-የተወሰኑ የሳንባ ችግሮች ለምሳሌ የሳንባ ደም ስር በደም መርጋት መዘጋት
-ከባድ አደጋ ፣ ውሃ ውስጥ መስመጥ ወይም ከባድ ኤሌክትሪክ አደጋ
-እንደ ኮኬይን ፣ ሄሮይን ወይም አምፊታሚን ያሉ ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች
- የሰውነት ንጥረ ነገሮች መዛባት / እንደ ሶዲየም ወይም ፖታስየም ያሉ ንጥረ ነገሮች መዛባት የልብን የኤሌክትሪክ ስራ መዛባት ያመጣሉ
የድንገተኛ የልብ ምት መቆም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ብዙ ሰዎች ከ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በፊት ምንም ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ላይኖራቸው ይችላል ነገር ግን የተወሰኑት ደግሞ ከ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በፊት ምልክቶች አሏቸው፡፡
እነዚህ ምልክቶች ከድንገተኛ የልብ ምት መቆም በፊት ወይም ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ባሉት ቀናት ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ምልክቶቹ የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ-:
- የደረት ህመም ወይም የመተንፈስ ችግር
- በጣም የመድከም ወይም የመዛል ስሜት
-ያልተለመደ የልብ በፍጥነት መምታ
-የእይታ መደብዘዝ
-ንቃተ ህሊናውን ማጣት ፣ እራስን መሳት ሊያስከትል ይችላል
ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ወዲያውኑ በሚከተሉት መንገዶች መታከም አለበት-:
1. Cardiopulmonary resuscitation ( CPR ) ልቡ መምታት ባቆመ ሰው አካል ውስጥ ደም እና ኦክስጅንን የሚያነቃቃ መንገድ ነው ፡ ይህም ሌላ ሰው ፈጣን የደረት ግፊትን በታማሚው ደረት ላይ በመጫን እና በአፉ አየር በመስጠት ልቡ እንደገና እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡
ከህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ ሁሉም ሰው የዚህ ድንገተኛ ህክምና ልምድ እንዲኖራቸው ይመከራል፡፡
2.Defibrillation ይህ በመሳሪያ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ህክምናን ወደ ልብ በመላክ የልብ ምት እንደገና እንዲጀምር ያደርጋል፡፡ Defibrillation ወዲያውኑ ሲከናወን ጥሩ ውጤት ለመስጠት ዕድል አለው፡፡
እነዚህ ሕክምናዎች በ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከተከናወኑ አንዳንድ ጊዜ ልብን እንደገና ለማስጀመር ይሰራሉ፡
በተጨማሪም ፡-
3.ብዙ ሰዎች የመተንፈሻ ቱቦ እና መተንፈቫ መሳርያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል
4. ሐኪሞች ወይም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አንዳንድ ጊዜ አካልን ለማቀዝቀዝ “hypothermia” የተባለ ሕክምና ይጀምራሉ. ይህ ሕክምና ከ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ሰዎች በሕይወት የመትረፍ እድል ይሰጣቸዋል.ይህ የአንጎል ጉዳትን ለመቀነስ ይረዳል. ምክንያቱም ከ ድንገተኛ የልብ ምት መቆም በኋላ የአንጎል ጉዳት ለሞት በጣም የተለመደ ምክንያት ነው፡፡
ልብ እንደገና መምታት ከጀመረ በሆላ የድንገተኛ የልብ ምት መቆም መንስኤን ለማወቅ እና ለይቶ ለማከም ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል እነዚህም ፡-
- ECG ወይም EKG – ይህ ምርመራ በልብዎ ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ለማወቅ ይረዳል
-የደረት ኤክስሬይ
- የደም ምርመራዎች
- Echocardiogram
- Coronary Angiography
ይህ ጽሁፍ ብዙ ግዜ ድንገተኛ ሞት ስለሚያስከትለው ድንገተኛ የልብ ምት መቆም የተወሰነ ግንዛቤ ለመፍጠር በቀላል አማርኛ የተጻፈ ሲሆን በሰዎች ሞት ላይ የሚሰነዘሩ የተለያዩ ሀሳቦችን በሚገባ ማጤን እና ሁሉንም ድንገተኛ ሞቶች ከህከምና ስህተት ጋር ማያያዝ ትክክል አለመሆኑን ለማስገንዘብ የተጻፈ ነው፡፡
እንዲሁም የህክምና ማህበራት የህብረተሰባችንን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ መድረኮችን መፍጠር ይኖርባቸዋል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
ዶ/ር ተመስገን አሰፋ
የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊሰት እና የደም ህክምና ፌሎ