07/11/2025
በሀዲያ ዞን የሾኔ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥ/ጽ/ቤት በወባ ወረርሽኝ መከላከልና አጎበር አጠቃቀም እንዲሁም የተፋጠነ ታላሚ ተኮር የህጻናት ክትባት ዘመቻ አፈፃፀም ሁሉም ባለድሻ አካላት በተገኙበት ገመገመ ።
*******ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም ****
በሀዲያ ዞን የሾኔ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥ/ጽ/ቤት በወባ ወረርሽኝን መከላከልና አጎበር አጠቃቀም እንዲሁም የተፋጠነ ታላሚ ተኮር የህጻናት ክትባት ዘመቻ ማጠቃለያ አፈፃፀም ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በመገምገም በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ውይይት አደረገ ።
በውይይት መድረኩ የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬን ጨምሮ የጤና ጽ/ቤት ኃላፊ እና ማኔጅመንት ፥ ከሆስፒታልና ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ፣ ከእናቶችና ህፃናት ፣ ከመረጃ ኦፊሰር እና ከጤና ኤክስቴንሽኖች ተሳትፈዋል።
የተፋጠነ ታላሚ ተኮር የህጻናት ክትባት ዘመቻ ሪፖርት በእናቶችና ህፃናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ በአቶ አማረ ማርቆስና የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ሪፖርት በጽ/ቤቱ ኃላፊ በአቶ ኤልያስ ዳዊት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል
በውይይት መድረኩ የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬ በክትባት ዘመቻው ይበል የሚያሰኝ ጠንካራ ስራ መሰራቱን አውስተው በቀጣይም በመደበኛው የክትባት ስራ ላይ አጠናክሮ በመስራት ባለመከተብ የሚመጡ ወረርሽኞችን መከላከል እንደሚገባ አሳስበው ከወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎችም ጋር ተያይዞ የሚታይ ስራ መሰራቱን ገልፀው አጎበር ያለው በአግባቡ እንዲጠቀም ማስተማር እንደሚገባ በመግለጽ የታመሙትንም መመርመርና ማከም እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሾኔ ከተማ አስተዳደር የጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ ዳዊት በበኩላቸው የተፋጠነ ታላሚ ተኮር የህጻናት ክትባት ዘመቻ ዋናው አላማ ክትባት ያልጀመሩትን ፈልጎ በማግኘት እንዲጀምሩ ማድረግ ፣ ክትባት ያቋረጡትን ማስቀጠል እና የሚዝል ክትባት በወቅቱ እዲወስዱ ማድረግና ሌሎችም በቅንጅት የሚሰሩ ስራዎችን አቀናጅቶ መስራት ሲሆን በዚህም አመርቂ ውጤት መምጣቱንና ለዚህም ስኬት በትጋትና በቁርጠኝነት የሰሩ ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑ ሲሆን በመልሶ ማረጋገጥም የተሻለ መሆኑን በመግለጽ ነገር ግን በዘመቻው የተገኙ ህፃናትን ተከታትሎ ክትባት ማስጨረስ እንደሚገባ አሳስበዋል ከወባ ጋር በተያያዘም ብቸኛው አማራጭ በተጀመረው መንገድ የአካባቢ ቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ መስራት ነው ያሉ ሲሆን ከአልጋ አጎበር አጠቃቀም ጋርም ተያይዞ ከ5 ዓመት ወዲህ ምንም አይነት የልጋ አጎበር ስርጭት እንዳልተደረገ አንስተው ህዝቡ በእጁ ያለውን እንዲጠቀም ማድረግ ይገባል በማለት በቀጣይም በቅንጅት ሁሉንም አይነት አደረጃጀት በመጠቀም የህዝባችንን ጤና መጠበቅ እንዲሁም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወባ ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ይገባል በማለት የተለያዩ የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎቹ ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ ከመድረክ ተሰጥቷል የእለቱ ፕሮግራም ተጠቃሏል።
ምንጭ:-የሾኔ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥ/ጽ/ቤት) ሾኔ
ሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ