01/11/2020
በአውሮፓ አገራት የኮቪድ-19 ስርጭት ጨምሯል
ኦስትሪያ እና ፖርቹጋል የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ አውጀዋል። እንግሊዝም ለአራት ሳምንታት የሚቆይ ገደብ እንደምትጥል አስታውቃለች።
የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በእንግሊዝ ለአራት ሳምንታት እንቅስቃሴ ይገታል ብለዋል።
ኦስትሪያ ውስጥ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ታውጇል። ካፌና ሬስቶራንቶች መስተንገዶ ከመስጠት ስለታገዱ ተጠቃሚዎች ባሉበት ምግብና መጠጥ ያደርሳሉ።
ባለፈው አርብ ኦስትሪያ በአንድ ቀን 5,627 በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች አግኝታለች። መንግሥት 6,000 ሰዎች በአንድ ቀን በቫይረሱ ከተያዙ ከህክምና መስጫዎች አቅም በላይ እንደሚሆን ተናግሯል።
አዲስ የተጣሉ የእቅስቃሴ ገደቦች እስከ ጥቅምት ማገባደጃ ይቆያሉ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘወተሪያ እና ሙዝየሞች ሲዘጉ፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች በበይነ መረብ ያስተምራሉ።
ፖርቹጋል የጣለችው ገደብ 70% የአገሪቱን ክፍል ያዳርሳል። ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት ወይም ለሌላ እጅግ አስፈላጊ ክንውን ካልሆነ በስተቀር ከቤት መውጣት አይችሉም።
በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ምን ላይ ይገኛል?
በኮቪድ-19 ማዕከላት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች የተገባልን ቃል አልተፈጸመም አሉ
በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 94 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ
የፖርቹጋል ጠቅላይ ሚንስትር አንቶንዩ ኮስታ፤ “ምንም እርምጃ የማንወስድ ከሆነ የጤና ሥርዓታችን ይንኮታኮታል” ብለዋል።
ትላንት በፖርቹጋል 4,007 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፤ 39 ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።
የተቀሩት የአውሮፓ አገራት
በአውሮፓ ያገረሸውን ቫይረስ ለመግታት ብዙ አገራተ እንቅስቃሴ ላይ ዳግመኛ ገደብ ጥለዋል።
ፈረንሳይ ባለፈው አርብ የታወጀውን ገደብ አስታውቃለች።
በሌላ በኩል ስሎቫኪያ ከአስር ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎችን ልትመረምር ነው። በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በተሰራጨባቸው አካባቢዎች ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሁለት ሳምንታት ይመረመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፖላንድ ውስጥ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
ህክምና እየተሰጣቸው ከሚገኙ 16,144 ሰዎች 1,305 ያህሉ በቬንትሌተር ታግዘው ነው የሚተነፍሱት።
ባለፈው ሳምንት ጽንስ ማቋረጥ በሕግ ሊከለከል መሆኑን በመቃወም ሰልፎች መካሄዳቸውን ተከትሎ የበሽታው ስርጭት እየተባባሰ ይገኛል።
ስብሰባዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ካፌዎችም እንዲዘጉ ተወስኗል።
የአገሪቱ ፕሬዘዳንት አንደርዛጅ ዱዳ ባለፈው ሳምንት ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ይፋ መደረጉም ይታወሳል።
በሌላዋ የአውሮፓ አገር ሀንጋሪ 51 ተጨማሪ ሰዎች ሞተው ቁጥሩ 1,750, መድረሱን መንግሥት ተናግሯል።
እስካሁን እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ባይጣልም፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቪክቶር ኦርባን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማያደርጉ ሰዎች በገንዝብ ይቀጣሉ ብለዋል።
በሀንጋሪ እስካሁን 71,413 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ግሪክ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች ሲሆን፤ ቤልጄም ደግሞ ዳግመኛ እንቅስቃሴ እንደሚገታ አስታውቃለች።
ከአውሮፓ አገራት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት በቤልጄም ነው።
BBC Amharic