03/17/2019
ካነበብኩት ስለ ወደድኩት
«ልብ ብለው ያንብቡት» ከወደዱት ለወዳጆ ያካፍሉ
፣
እኔና ጓደኛዬ ከስራ በኋላ ተገናኝተን መኪና ውስጥ ሻይ እየጠጣን እያወጋን ነበር ፤ በድንገት የመኪናችን መስኮት በር ተንኳኳ ። ጎስቆል ያሉ አዛውንት ልጆቼ አንድ ብር ስጡኝ ? ብለው የተማፅኖ ቃና በሌለው አኳኋን ጠየቁን ፡፡ ስጡኝ የምትለው ቃል ትንሽ ደስ ባትልም ጓደኛዬ ከአፍታ ማቅማማት በኋላ ከኪሱ አንድ ብር አውጥቶ ሰጣቸውና ጠጡበት ደግሞ" አላቸው ።
፣
ሽማግሌው የኔ ቢጤ ምን ብለው ቢመልሱ ጥሩ ነው ? አይ ! የለም ቤት እሰራበታለሁ ! እኔም ሆንኩ ጓደኛዬ ፈፅሞ ያልጠበቅነው መልስ በመሆኑ በሳቅ ፈረስን ሳቄን ለመቆጣጠር እየሞከርኩ ። ፋዘር ምን ለማለት ፈልገው ነው ? ስል ጠየቅኳቸው ፤ እንዴ ! ጓደኛህ እራሱ ምን ለማለት ፈልጎ ነው ? በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ብር ነው የሰጠኝ ።
፣
ታዲያ በዚህ አንድ ብር ምን እንዳረግበት አስቦ ነው ? ሲቀጥል ብሩን ከመስጠቱ በፊት ምን ልታደርግበት ነው ብሎ አልጠየቀኝም ፤ ታዲያ ከሰጠኝ በኋላ ምንስ ባደርግበት ብሩም፣ ነፃ ፈቃዱም የኔ አይደል እንዴ ? ምን ገዶት ያዘኛል በገዛ ብሬ?የሽማግሌው መልስ በአንድ በኩል ትክክል ነው ፤ ሎጂካል ነው ፤ በሌላ በኩል ግን ድፍረታቸውና ግልፅነታቸው ገረመኝ ። ጓደኛዬ ቀጠለ እሺ አሁን ልጠይቆት ምን ሊያደርጉበት ነው ? ልጠጣበት ! አሉ ሽማግሌው ቀለል አድርገው አሁንም ሳቄ አመለጠኝ ።
፣
እውነቶትን ነው ? አልኳቸው ፡፡ እውነቴን ነው እንጂ ልጄ በዚህ እድሜዬ ለምን እዋሻለው ። አሁንም በምላሻቸው ተገርሜ ምግብ በልተዋል ? ስል ጠየቅኳቸው ቁርስ በልቻለው አሉኝ አሁን እኮ እራት ሰዓት ነው ፤ አልራቦትም ? መራቡንስ ርቦኛል ግና የሌሊቱን ብርድ ከነረሃቤ ስለማልችለው ነው አረቄየን የምጠጣው ውስጤን ለማሞቅ ፤ አየህ ! እናንተ ሁለቱንም ማድረግ ትችላላችሁ ።
፣
እስኪበቃችሁ እራታችሁን መብላት እንዲሁም መጠጣት እኔ ግን አንዱን መምረጥ አለብኝ ፤ ስለዚህ የእንቅልፍ ኪኒናዬን አረቄዬን ጠጥቼ ለጥ እላለኋ የሽማግሌው ንግግር እኔና ጓደኛዬ ሆድ ውስጥ እኩል ዘልቆ የገባ ይመስል ሁለታችንም እኩል ቀና ብለን ተያየን በአይን ቋንቋ ብቻም ተግባባን ።
፣
ፋዘር መኪናው ውስጥ ይግቡ ፤ እኛ እራት ልንበላ ስለሆነ አብረን እንበላለን ፤ በዛውም ጨዋታዎት ደስ ስላለን አንድ ፣ ሁለት እያለን እናወጋለን ሽማግሌው መኪናው ውስጥ ላለመግባት አምባ ጓሮ ፈጥሩ ። የለም ! መኪናችሁን አቆሽሽባችኋለው ። በመከራ አሳመንናቸውና ከኋላ ገብተው ተሳቀው ተቀመጡ (ቁጢጥ አሉ ማለት ይቀላል) ።
፣
በቅርብ ወደሚገኝ አንድ ሬስቶራን አመራን ሽማግሌው የኔ ቢጤ ስማቸው ጋሽ በቀለ እንደሆነ ነገሩን እኛ ግን ወዲያው ጋሽ በቄ ብለን ጠራናቸው ። መኪናችንን አንድ ምግብ ቤት ግቢ ውስጥ አቁመን ወደ ሬስቶራንቱ ልንገባ ስንል ። የሬስቶራንቱ ጥበቃ "ወዴት ነው ! ብሎ ጋሽ በቄ ላይ አፈጠጠባቸው ። ጓደኛዬ በንዴት ቦግ ብሎ ከኛ ጋር ናቸው ! ብሎት ገፍትሮት ለመግባት ሞከረ ።
፣
ይህን ጊዜ ሁኔታችንን ከውስጥ ሆኖ ይከታተል የነበረ የሬስቶራንቱ ማኔጀር ጥድፍ ፣ ጥድፍ እያለ ወደኛ መጣ ይቅርታ ችግር አለ ? ሲል ጠየቀ ጥበቃው ቀልጠፍ ብሎ ለማኔጀሩ በጆሮው የሆነ ነገር ሹክ አለው ። ማኔጀሩም ትንሽ ካቅማማ በኋላ ይቅርታ ወንድሞቼ ሬስቶራንት ውስጥ ትልልቅ እንግዶች ስላሉ ውጪ ላይ መቀመጥ ትችላላችሁ ? ሲል በተማፅኖ እጅ ነሳ ። ይህን ጊዜ ጓደኛዬ ይብሱኑ ቱግ ብሎ እኛ ትንሽ ነን ? ለምን ! የቆሸሸ ልብስ ስለለበሱ ነው! ትልቅነት የሚለካው በአለባበስ ነው ? በጣም ያሳዝናል ። ጋሽ በቄ በፍፁም እርጋታና በብስለት ፈገግታ የጓደኛዬን ትከሻ መታ መታ እያደረጉ ተዋቸው ልጄ እነሱ እኮ የታዘዙትን የሚፈፅሙት ፤ ከህሊናቸው በላይ ደሞዛቸው ስለሚጠቅማቸው ነው ። አትፍረድባቸው ።
፣
አንተ እንዳልከው ትልቅነት በገንዘብና በቁስ የሚለካ አይደለም ፤ የሰው ትልቅነቱ የሚለካው በአይምሮው ነው ፤ በብስለቱ ! ያ ብስለቱ ደግሞ ሁሉን ንቆና ስቆ እንዲያልፍ ሊያስችለው ይገባል ። ጋሽ በቄ ከፊታችን እየተራመዱ ግድ የለም ኑ ! ለኛም የውጪው አየር ይሻለናል እዚህ በነፃነት እንጫወታለን አየሩም ግሩም ነው ብለው አንድ ጥግ ላይ ወዳለ ጠረጴዛ መኖሩን የጋሽ በቄ እርጋታና አስተዋየነት ከእድሜያቸው የሚጠበቅ ቢሆንም የእርሳቸው ግን ለየት ያለ ነው ።
፣
ፍፁም ቅን ፣ የዋህና ብሱል ናቸው በነገሮች ቶሎ አይደነቁም ፣ ቶሎም ቅር አይሰኙም ። እራታችንን በአንድ ትሪ ተቋድሰን ቢራችንን እየጠጣን ጋሽ በቄ ስለ ህይወታቸው አጫወቱን ልጆቼ ! በአንድ ወቅት እኔም እንደናንተው የራሴ ስራ የነበረኝ ትንሽም ብትሆን ደሞዝ ተከፋይ ነበርኩ ለብቻዬ ቤት ተከራይቼም እኖር ነበር በአንድ ክፉ ቀን ከሃላዬ የመጣ መኪና ድጦኝ እግሬ ተሰበረ እናም ለረጅም ወራት ሆስፒታል ተኛሁ ።
፣
ታዲያ በጥበቃነት የምሰራበት መስሪያ ቤት ለተወሰነ ጊዜ ደሞዜን እየከፈለ ቢያሳክመኝም ቶሎ ባለማገገሜ የነሳ በኔ ቦታ ሰው ተክተው በየወሩ የሚሰጡኝንም ትንሽ ብር አቋረጡብኝ አከራዮቼም በሌለሁበት ቤቴን አሰብረው እቃዬን አውጥተው ክፍሌን አከራዩት ታዲያ የቅርብ ዘመድም ሆነ ጓደኛ ስላልነበረኝ
በክራንች ድጋፍ መንቀሳቀስ ስጀምር ከሆስፒታል ወጥቼ ጎዳና ላይ መኖር ጀመርኩ ይገርማል !
፣
በአንዲት አጋጣሚ ህይወቴ እንዲህ ሆነ ። ይኸው እስከዛሬ እዚሁ ጎዳና አለሁ " አንድ ሁለት ቢራ እያልን የጋሽ በቄን አፍ የሚያስከፍት ታሪክ ተመስጠን ስንሰማ ሳናስበው ሰዓቱ ስለሄደብን ጋሽ በቄን ወደ ቦታቸው ሸኝተናቸው ለመለያየት ተስማማንና ወደ መኪናችን ተመለስን መኪና ውስጥ እንደገባን ጓደኛዬ የተወሰነ ብር አውጥቶ ጋሽ በቄ እቺን ይያዟት ሲላቸው ጋሽ በቄ ወደ ኋላቸው ሽምቅቅ ብለው በግርምት ጓደኛዬን እየተመለከቱት ለምኔ ነው ብር የምትሰጠኝ ? እስክጠግብ እራቴን በልቼ የሚበቃኝን ያህል ጠጥቼ ከዚህ በኋላ ብር ምን ሊያደርግልኝ ነው ?
፣
"አይ ለነገ ይሆኖታል አልኩ ቀልጠፍ ብዬ ይሄን ጊዜ ጋሽ በቄ ያን የብስል ፈገግታቸውን ብልጭ አድርገው ጎዳና ካስተማረኝ ነገሮች አንዱ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ልጆቼ ? የኛን መልስ ሳይጠብቁ ንግግቸውን ቀጠሉ ። ጎዳና ካስተማረኝ ነገር አንዱ ስለ ዛሬ ብቻ መኖርን ነው ። የጎዳና ኑሮን በቅጡ ከተረዳሁበት ቀን ጀምሮ ገንዘብ ይዤ ተኝቼ አላውቅም እራቴን በልቼና አረቄዬን ጠጥቼ ብር ከተረፈኝ የቀረኝን ገንዘብ ለሌላ የኔ ቢጤ ሰጥቼ እተኛለሁ እንጂ በኪሴ ገንዘብ ይዤ ተኝቼ አላውቅም ።
፣
እኔ ገንዘብ በኬሴ ይዤ ተኝቼ ስለምን ሌላው ወንድሜ ፆሙን ያድራል ? የቤት ኪራይ የለብኝ ፣ ግብር አልከፍል ፣ የመብራት ፣ የውሃ አልል ለምን ብዬስ ብር አጠራቅማለው ? የዕለት ጉርሴን ካገኘሁ ተመስጌን ብዬ መተኛት ነው እንጂ ልጆቼ እያንዳንዷ ቀን የራሷ ዕድል አላት ! መጥፎም ይሁን ጥሩ ። እኛ ሰዎች ማለት ፣ አይናችንን በመሃረብ የተጋረድን አይነት ፣ በደመነብስ የምንጓዝ እንስሳ ማለት ነን ።
፣
ከፊታችን ያለውን የማናይ የነገን የማናውቅ ህይወታችንን እኛ የምንመራት ይመስለናል ፤ ዳሩ ግን ህይወት የራሷ መንገድ አላት በራሷ መንገድም እራሷ ትመራናለች ይሄ ነው
በእኔ ህይወትም የሆነው የእኔን ህይወት የቀየረቻት አንዲት ክፉ አጋጣሚ ናት ፤ እንዲህ እሆናለው ብዬ አንድም ቀን አስቤ
አላውቅም ነበር ።
፣
"በሉ ሂዱ ልጆቼ እንዳይመሽባች እኔ አንዴ ወሬ ከጀመርኩ አላቆምም ጋሽ በቄ በሩን ከፍተው ከወጡ በኋላ መረቁን ልጆቼ እግዜር ይስጣችሁ ያሰባችሁት ድረሱ ለኔ በጎ እንዳደረጋችሁ በሄዳችሁበት ሁሉ በጎ ይግጠማችሁ በመጨረሻ ግን አንድ ነገር ልበላችሁ ። እኛ ሰዎች ሀሳባችን ብዙ ነው ። አንዳንድ ጊዜ አላፊዎች መሆናችንን እንረሳለን ሸክላዎች ከአፈር የተሰራን ብናኝ አመዶች መሆናችን እንረሳለን እናም ህይወት በሌለው ህይወት እንጠመዳለን አዎን ትልቁን ቁም ነገር- ቅንነትን ፣ ደግነትንና ፍቅርን እረስተን ዘላለም ለማንኖርባት ምድራዊ ድሎት እንሰርቃለን እንዋሻለን እናጎበድዳለን ።
፣
እርስ በርስ እንጣላለን እንገዳደላልን በራስ ወዳድነት በስግግብነትና በጨፍንነት እድሜያችንን እንፈጃለን ስለነገ የዛሬን ብሩህ ቀን ቀለም በቆሻሻ ስብዕና እናጎድፋለን ። ይህን ስላችሁ ስለ ነገ አታቅዱ አታስቡ ማለቴ አይደለም ! ነገር ግን የነገን የማታውቁ መሆናችሁን በማሰብ እያንዳንዷ ዛሬያችሁን በጥሩነት ኑሩ ጥሩ አድርጉ ያኔ ጥሩ ህይወት ባይኖራችሁ እንኳን ጥሩ ህሊና ይኖራችኋል ። ለስጋ ከመኖር በላይ ለህሊና እንደ መኖር እረፍት የሚሰጥ ነገር የለምና ።
፣
ጋሽ በቄ በሩን ዘግተው በዝግታ ወደ ማደሪያቸው አዘገሙ ። ሰው ባሰበበት አይውለም! ማለት እንዲህ ነው ። ፈፅሞ ያላሰብነው ምሽት ፤ ነገር ግን ጋሽ በቄ እንዳሉት በዚች ከንቱ ህይወት በሚሏት ዙረት ስንባክን እረስተናቸው የነበሩ ቁልፍ የህይወት መርሆዎችን አስታወሱን- ጥሩነት ፣ ፍቅርና ቅንነት ። ጓደኛዬ ከጋሽ በቄ ጋር ግንኙነቱን ቀጥሎ ጓደኛሞች ሆነው ነበር ። ሲከፋው ምክር ሲፈልግ እሳቸው ጋር ይሄዳል ።
፣
ጋሽ በቄ አሁን በህይወት የሉም ። ጆሮና ጊዜ ሰጥተን ብንሰማቸው እንደ ጋሽ በቄ አይነት ብዙ የሚያስደምም ፍልስፍናና ነብስ ያላቸው ሰዎች ግን በየጉዳናው ይኖራሉ ።
፣
«ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያካፍሉ»